ያሬድ ክብር አነሰው
ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . ሰውም ሳይሰፍርባት አሜሪካ ታውቃ፣
ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . . . እንዲህ ሳትሠለጥን አውሮፓም ተራቅቃ፣
ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . . ዓለም፣ ከእንቅልፏ ሳትነቃ፣
እነ ሞዛርት እና እነ ቤትሆቨን፣ የዜማን ምልክት ገና ሳይነግሩን፣
ያሬድ አንተ ነበርክ የዜማን ቅማሬ የሠራህልን፣ . . . .
መንኮራኩር ሠርተው ጨረቃ ላይ ወጥተው፣ አፈር ስላመጡ ዓለም ተደነቀ፣]
ወሬው ተሟሟቀ፣ . . . .
ከምዕራብ ተነሥቶ ከምሥራቅ ዘለቀ፣ . . . .
ከሺ ዓመት በፊት ግን ያሬድ የተባለ አንደ ሊቅ ነበረ፣ . . . .
ጨረቃንም አልፎ ጠፈር ተሻገረ፣ . . . .
ሐኖስን ሰንጥቆ ሰማያት ውስጥ ገብቶ፣ . . . .
አስደናቂ ዜማ ከመላእክት ሰምቶ፣ . . . .
አኩስም ላይ አዜመው ከጽናጽል እና ከመቋሚያ አስማምቶ፣ . . . .
ግና ምን ያደርጋል . . . . . . . ከጨረቃ አፈር የሚበልጥ ነገር፣ . . . .
ጨረቃም ላይ ካለው የሚበልጥ ምሥጢር፣ ያሬድ ይዞ መጥቶ፣ . . . .
የሚናገር እና የሚያደንቅ ጠፍቶ፣ . . . .
ዓለም አያውቀውም አልሰማውም ከቶ፣ . . . .
ያሬድ ግን ቅዱስ ነው ያሬድ ምሁር ሊቅ፣ . . . .
ያሬድ መተርጉም ነው ምሥጢር የሚያረቅቅ፣ . . . .
ያሬድ ፈላስፋ ነው ያሬድ ባለ ቅኔ፣ . . . .
ያሬድ ባለ ዜማ የዜማው መጣኔ፣ . . . .
ያሬድ ሐጋጊ ነው ሥርዓት የሠራ፣ . . . .
ያሬድ መምህር ነው ዕውቀትን ያበራ፣ . . . .
ያሬድ ቀማሚ ነው ብሉይ ከሐዲስ፣ . . . .
ያሬድ ሰባኪ ነው ነፍስ የሚመልስ፣ . . . .
ያሬድ አመልካች ነው ኖታን የፈጠረ፣ . . . .
ያሬድ መናኒ ነው በጸሎት የኖረ፣ . . . .
እነ ቸርችል፣ ፑሽኪን እና ካኒንግሃም አደባባይ መንገድ ሲሰየምላቸው፣
ያሬድን ስላጡት አዘነ ልባቸው፣ . . . .
ነቢይ በሀገሩ አይከብርም እንዲሉ፣ . . . .
እኒህ ኢትዮጵያውያን እጅግ ይሞኛሉ፣ . . . .
የእጃቸውን ንቀው ሌላ ያከብራሉ፣ . . . .
ብለው አዘኑብን በፈጸምነው ግፍ፣ . . . .
ያሬድን ረስተን ሌላውን ስናቅፍ፣ . . . .
አይበቃም ወይ ታድያ የሞኝነት ኑሮ፣ . . . .
መቅረት አለበት ወይ ታሪኩ ተቀብሮ፣ . . . .
ይተረክ ታሪኩ ይነገር ዝናው፣ . . . .
ይጠና ይመርመር ይታወቅ ሥራው፣ . . . .
መወያያ ይሁን በየሚዲያው፣ . . . .
መማማርያ ይሁን ትውልድ ያድንቀው፣ . . . .
ያለበለዚያ ግን ያለፉትን ንቀን ወደፊት ብንሄድ፣ . . . .
እኛንም የሚንቅ ይመጣል ትውልድ .
በዲ.ዳንኤል ክብረት
. . .
No comments:
Post a Comment