Wednesday, June 10, 2015

"መኖር እንዲህ ነበር"

"መኖር እንዲህ ነበር"
ገና ሲወለዱ ይችን ምድር ሲያዩ፣
የዓለምን ጣዕምና ምሬቷን ሳይለዩ፣
መኖር እንዲህ ነበር ጌታን ብቻ እያዩ።
ገና በማለዳ ገና በጠዋቱ፣
ገና ቀትር ሳይሆን ሳይመጣ ምሽቱ፣
ገና ሳይሰለጥን ጨለማው ሌሊቱ፣
ገና ብርሃን ሳለ ሥራን ሳይታክቱ፣
መኖር እንዲህ ነበር እንዲያርግ ጸሎቱ።
በዓለም ያለውን ዓለምን ሳይወዱ፣
ዓለምን አግብቶ ሌላ ዓለም ሳይወልዱ፣
መኖር ይሻል ነበር ለአንተ መሰደዱ።
በጸሎት በስግደት በፆም ተጋድሎ፣
ሰይጣንን ድል ነስቶ ወደ ጥልቁ ጥሎ፣
መኖር እንዲህ ነበር አንተን ብቻ ብሎ።
ገዳሙ ገዳሙ ሰምተሃል? ገዳሙ፣
ለልማት ይመንጠር ብሎሃል ዓለሙ።
በዚህ ትስማማለህ? መልስ ስጥ ገዳሙ፣
ልማት አይደለም ወይ? ጸሎቱና ፆሙ።
ይህንን ከመስማት ደግሞም ከማየት፣
የዓለምን ጥላቻ ኩርፊያ ለመርሳት፣
ለኃጢአት ሞተን ኖረን ለሕይወት፣
መኖር እንዲህ ነበር መንኖ በእውነት።
ከቀሲስ ዲበኩሉ በላይ
ግንቦት 29/2007

Saturday, August 9, 2014

Why We Sometimes Write "Etc" In Exams?
Because It Means.
.
.
.
E-End Of
T-Thinking
C-Capacity

But Teacher Won't Ever Understand Our FEelings...

 

WHY STUDENT FAIL
Sundays-52 in a year,Days left 313
Summer holidays 50,Days left 263
8 hrs daily sleep-130 days GONe, Days left 141
1 hr daily playing means 15 days,Days left 126
2 hrs daily for eating means 30 days.Days left 96,
1 hr talking means 15 days.,Days left 81
Exams days 35 days,Days left 46
Eid & Gov holidays 20, Days left 26
Movies,TV at least 25 days,Days left 1
That 1 day is your BIRTHDAY.

 

Question by a student !!
If a single teacher can't
teach us all the subjects,
Then...
How could you expect a single student
to learn all subjects ?

 

Thursday, August 7, 2014

ንሥር BY DANIEL KIBRET

ንሥር እጅግ ግዙፍ ከሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡ ክብደቱ እስከ 6.7 ኪሎ ሲደርስ ቁመቱ ደግሞ ከአንዱ ክንፉ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ 2 ሜትር ተኩል ይደርሳል፡፡ በዓለም ላይ እስከ ስድሳ የሚደርሱ የንሥር ዝርያዎች ይገኛሉ፡

በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ንሥር የትንሣኤ ሙታን፣ አርቆ የማሰብ፣ ወደ ላይ የመምጠቅና የመነጠቅ፣ የጥበቃና የምናኔ ተምሳሌት ሆኖ ተገልጧል፡፡ ግብጻውያን ደግሞ የተቀበሩ ሰዎችን አጋንንት እንዳይደርሱባቸው በመቃብራቸው በር በድንጋይ ላይ የንሥርን ምስል ያስቀርጹ ነበር፡፡ ይጠብቃቸዋል ብለው፡፡ በግሪክ አፈ ታሪክ የአማልክት ንጉሥ የሚባለው ዜውስ በንሥር የሚመሰል ነበር፡፡ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች እጅግ ለሚያከብሩት የሌላ ወገን ሰው የንሥርን ላባ በመስጠት ክብራቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጡ ነበር፡፡ ሞቼ የተባሉት የፔሩ ሕዝቦችም ንሥርን ያመልኩት ነበር ይባላል፡፡


ንሥር ይህንን ያህል ቦታ በሕዝቦች ባሕል ውስጥ ሊይዝ የቻለው በተፈጥሮው በታደላቸው የተለያዩ ጸጋዎች የተነሣ ነው፡፡
ንሥር ከእንስሳት ሁሉ ወደ ሰማይ በመነጠቅ የሚተካከለው የለም፡፡ እርሱ የሚደርስበትን የሕዋ ከፍታ የትኛውም ዓይነት ወፍ አይደርስበትም፡፡ አንዳንድ አዕዋፍ እስከ ተወሰነ ድረስ ቢከተሉትም እንኳ እርሱ ግን ጥሏቸው ማንም በማይደርስበት የሰማይ ጥግ ብቻውን ይንሸራሸራል፡፡ ለዚህም ነው ጥንታውያን ሰዎች በሐሳብ የመምጠቅ፣ ማንም ከማይደርስበት የጸጥታ ሕዋ ላይ አእምሮን የማሳረግ፣ ተራ ነገር ማሰብና ተራ ነገር መሥራት ከሚችሉ ደካማ ልቦች ርቆ በሉዓላዊ ሐሳብ ላይ የመምጠቅ ምሳሌ ያደረጉት፡፡


ታድያ ይኼ ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ከቁራዎችና፣ ከሌሊት ወፎች፣ ከጥንብ አናሣዎችና ከድንቢጦች፣ ከተባዮችና ከነፍሳት ጋር እዚህ ምን ታደርጋለህ? በወረደ ሐሳብ ለምን ትመስላቸዋለህ? ውጣ ወደላይ፤ ሂድ ዐርግ፣ ምጠቅ ተመሰጥ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስ ዝንብና ትንኝ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስም ነፍሳት፣ እስከ ተወሰነም ቦታ ድንቢጦችና የሌሊት ወፎች፣ እስከ ተወሰነውም ቁራዎችና ጥንብ አንሣዎች ይከተሉህ ይሆናል፡፡ ሐሳብህን ከፍ፣ አእምሮህንም ሉዓላዊ፣ ልቡናህንም ምጡቅ፣ አመለካከትህንም ከፍ ያለ ባደረግከው ቁጥር ግን ደካቹ ከሥር እየቀሩ ከሚመስሉህ ከንሥሮች ጋር ብቻ በጸጥታው ሕዋ ላይ ትንሳፈፋለህ፡፤ ሂድ ዐርግ፡፡


ንሥር እጅግ አስደናቂ የሆነ የማየት ችሎታ የተሰጠው ፍጡር ነው፡፡ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ውስጥ አንዲትን ትንሽ ጥንቸልን አንጥሮ ማየት ይችላል፡፡ የንሥር ዓይን ከጭንቅላቱ በተነጻጻሪ ሲታይ እጅግ ታላቅ ነው፡፡በንሥር ዓይን ውስጥ በአንድ ሚሊ ሜትር ስኩዌር ረቲና አንድ ሚሊዮን ለብርሃን ስሱ የሆኑ ሴሎች አሉት፡፡ ሰዎች ስንት ያለን ይመስላችኋል? ሁለት መቶ ሺ ብቻ፡፡ የንሥር አንድ አምስተኛ ማለት ነው፡፡ ሰው ሦስቱን መሠረታዊ ቀለሞች ብቻ ማየት ሲችል ንሥር ግን አምስቱን ማየት ይቻለዋል፡፡ እንዲያውም ከሩቁ አንጥሮ በማየት ንሥርን የሚተካከለው እንስሳ የለም የሚሉ ጥናቶችም አሉ፡፡


ንሥር የሚፈልገውን ለማሰስ እስከ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ ይዞራል፡፡ ሲያገኝ ግን ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ በሚያድነው ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት› የሚለውን የአማርኛ ብሂልና ‹jack of every thing master of non› የሚለውን የእንግሊዝኛ አባባል በደመ ነፍስ ዐውቆታል፡፡ ከትኩረቱ ፈጽሞ ንቅንቅ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ግርዶሽ፣ ምንም ዓይነት መሰናክል፣ ምን ዓይነት መደለያ አያዘናጋውም፣ ተስፋም አያስቆርጠውም፡፡ የዚያን የአደኑን ነገር በንቃትና በትጋት እስከ መጨረሻ ይከታተለዋል፡፡ እንዲሁ አይወረወርም፤ ጊዜና ሁኔታ ይመርጣል፡፡ ጊዜና ሁኔታ ሲገጥሙለት ትኩረቱን ሰብስቦ በመወርወር ታዳኙን ይሞጨልፈዋል፡፡


ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ደጋግመህ አስብ፤ ለመወሰን ጊዜ ውሰድ፤ ዙር ተዟዟር፡፡ ልፋ ድከም፤ አንድ ጊዜ ለመቁረጥ ሺ ጊዜ ለካ፡፡ በመጨረሻም ዒላማህን ለይ፡፡ አስተካክል፡፡ ትኩረትህንም በዒላማህ ላይ ብቻ አድርግ፤ ምንም ዓይነት ማታለያ፣ ምንም ዓይነት መደለያ፣ ምንም ዓይነት ማሰናከያ፣ ምንም ዓይነት ፈተና፣ ምንም ዓይነት ተስፋ መቁረጥ ከዓላማህ ሊያግድህ አይገባም፡፡ ማየትና ማሰብ ያለብህ ሁሉም ሊያየውና ሊያስበው የሚችለውን ተራ ነገር አይደለም፡፡ ሊታይ የማይችለውን ለማየት፣ ሊለይ የማይችለውን ለመለየት፣ ሊተኮርበት ያልቻለውን ለማተኮር ጣር፡፡ ዒላማህን ካገኘህ አትልቀቅ፤ ጊዜና ሁኔታ አመቻችና ዒላማህ ላይ ተወርወር፡፡ ያንተ ከመሆን ማንም አያግደውም፡፡


ንሥር በምንም ዓይነት የሞቱ እንስሳትን አይበላም፡፡ እርሱ እቴ፡፡ በሕይወት ያለውን እንስሳ የገባበት አሳድዶ፣ ከተደበቀበት ጠብቆ አድኖ ይበላዋል እንጂ እርሱ እንደ ቁራና ጥንብ አንሣ የሞተ ላይ አያንዣብብም፡፡ እንደ አራዳ ልጆች ከተበላ ዕቁብ ጋር አይጨቃጨቅም፡፡ ቀላል ነገር ቢያጣ በግና ፍየልም ቢሆን ተወርውሮ አድኖ፣ ከዐለት ላይ ፈጥፍጦ እንደ አጥንት ወዳጅ አበሻ ቅልጥም ሰብሮ ይበላል እንጂ የሞተ ጥንብ ሲያልፍም አይነካው፡፡ ያቺን ከባዷንና በድንጋይ የተሸፈነችውን ዔሊ እንኳን ከዐለት ስባሪ ላይ ከስክሶ ድንጋይዋን አራግፎ ይበላታል እንጂ  እንደ አበሻ ማን እንዳረደው ያላወቀውን ነገር አይበላም፡፡


ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ልቡናህንና ኅሊናህን፣ አእምሮህንና መንፈስህን ምን እንደምትመግባቸው አስብ፡፡ የሞተ፣ የማይሠራ፣ የተበላሸ፣ ጊዜው ያለፈበት፣ ቁራና ጥንብ አንሣ የሚጫወቱበትን አትመግበው፡፡ ፊልምና ፕሮፓጋንዳ፣ ዋዛና ፈዛዛ፣ የወረዱና የበከቱ አስተሳሰቦችን አትመግበው፡፡ ከተፋና ለብለብ ሐሳቦችን አትጋተው፡፡ ይልቅ አድን፣ ድከም፣ ልፋ፣ ተሟገት፣ ተመራመር፣ እንደ ዔሊ ድንጋይ የከበደውን አስተሳሰብ ገልብጠህ፣ ፈንክተህ ተመገብ፤ ድካምና፣ ጽሞና፤ ማሰብና መመርመር የሚሻውን ንባብ ውደድ፤ ሳይለፉና ሳይደክሙ እንደ ሞተ እንስሳ ሥጋ የትም የሚገኘውን ነገር ሳይሆን ጥረትና ግረት የሚሻውን፤ ላብ ጠብ የሚያደርገውን ሞያና እንጀራ ፈልግ፡፡


ንሥር ዐውሎ ይወዳል፡፡ ሰማዩ ሲጠቁርና ደመናው ሲሰበሰብ ወጀቡም ሲያይል ሌሎች አዕዋፍ በዐለት ንቃቃትና በጫካው ችፍርግ ውስጥ ይደበቃሉ፤ በቤት ታዛ ሥርም ይሠወራሉ፡፡ ንሥር ግን ደስ ይለዋል፡፡ ወጀቡና ዐውሎው ሲጀምር ንሥር የንፋሱን ኃይል በመሞገት የራሱን ጥንካሬ ይለካበታል፡፡ የነፋሱን አቅጣጫ በመከተልም ይበራል፡፡ ራሱን ወደ ላይ ለማምጠቅና የከፍታውን ጫፍ ለመጨበጥ ይጠቀምበታል፡፡ በዚያ ጠንካራ ነፋስ ትከሻ ላይ ሲጫን ነው ንሥር ዕረፍት የሚወስደው፡፡ ክንፉን ብቻ ዘርግቶ በዕረፍት ስሜት ከደመና በላይ የኃያሉን ዐውሎ ዐቅም ተጠቅሞ ይንሸራሸራል፡፡


አንተንም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- መከራንና ፈተናን አትፍራ፤ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥም ቢሆን መንገድ አለና፡፡ መከራውንና ችግሩን፤ ፈተናውንና ግብግቡን የአዳዲስ ሐሳቦች መነሻ፤ የጥንካሬህ መለኪያ፤ ዐቅምህን የምትሰበስብበት አጋጣሚ፣ ወደላይ የምትመጥቅበትና ከችግር ደመናዎች በላይ የምትንሳፈፍበት ዕድል አድርገው፡፡ እንደ ሌሎች ወፎች ከመከራው አትሽሽ፤ ከችግሩም አትደበቅ፤ መከራን ለበረከት ተጠቀምበት፡፡

ለእግዜር የተላከ ደብዳቤ

ለእግዜር የተላከ ደብዳቤ
(ገጣሚ ጌታቸው ይመር )
----------------------
እንደምነህ እግዜር
ሰማይ ቤት እንዴት ነው
እመጣለሁ ብለህ ቆየህሳ ምነው?

እኛማ.....
ለእልፍ አላፍ አለቃ
ማመልከቻ ፅፈን
ለወፈ ሰማይ ህዝብ
መድረክ ላይ ለፍፈን
ፆለት ቤታችንን
እኛው ላይ ቆልፈን
የምድር አተካራ
ህግጋቱን አልፈን ደብዳቤ ላክንልህ፤

አይንህን ካየነው
ሁለት ሽ ዘመን
እንደቀልድ አለፈ
የመምጣትህ ተስፋ እየኮሰመነ
መቅረትህ ገዘፈ...

እንደውም እንደውም...
‹‹በእመጣለሁ ተስፋ
ሁለት ሽ ዘመን
ቀጥሮን ከጠፋ
በቀጠሮው ሰአት
መምጣት ከተሳነው
እግዜር አበሻ ነው›› እያሉ ያሙሃል

እኔ ምን አውቃለሁ...
አመስግነው ሲሉ እልልታ የማቀልጥ
ቃሉን ስማ ሲሉኝ ...ሰባኪው እግር ስር በደስታ እምቀመጥ
እግዚኦ በሉ ሲባል ...እንባየን የማፈስ
ሃሌ ሉያ ሲሉኝ ...በሳቅ ልቤ እሚፈርስ
ምናምኒት እውቀት ውስጤ ያልፀደቀ
እንበረከክበት ጉልበቴ ያለቀ
እኔ ምን አውቃለሁ...

ግን አንተ ደህና ነህ?
ከምር እንደሚያሙት ምፅአት ቀረ እንዴ ?
የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አትከፋም አንዳንዴ!

ከሆነስ ሆነና ሰማይ ቤት እንዴት ነው
አብረሃም ሰላም ነው...
እዛስ ቤት ገነባ ዛሬም በድንኳን ነው ?

እኛማ ይሄውልህ...
በቤት ኪራይ ችንካር እየተሰቀልን
‹‹ኤሎሄ›› እንላለን ጎጆ እንድጥልልን....
ወደላይ ገነባን ወደጎን አሰፋን
ወደላይም ከላይ ወደጎንም ከጎን
እንደጉድ ተገፋን
ቤት ለእንግዳ ማለት ጭራሹኑ ጠፋን !!

አባታችን ሙሴ እነዴት ነው ለክብሩ
ውቂያኖስ መክፈያው ደህናናት ብትሩ?

እኛማ ይሄውልህ....
እንጀራ ፍለጋ ባህር ስናቋርጥ
የተስፋዋን ምድር አሸዋ ሳንረግጥ
የትም ውሃ በላን የትም አሳ ላሰን
ን ገ ር ል ን ና ብትሩን ያውሰን....

እናልህ እግዜር ሆይ....
ከተስፋዋ ምድር ወደሌላ ተስፋ አለን እየኳተን
መሄጃው ሲገርመን መመለሻ መንገድ መቆሚያ ቦታ አጥተን...!

ላባታችን ሙሴ እንደምትልልን...
‹‹የመሄድ ዘመን ነው
ባህር የመሻገር
‹‹ዱላህን ላክልን›› ብሎሃል በልልኝ...

ሰማይ ቤት እንዴት ነው? ....ዳዊትስ ደህና ነው?
ዛሬም ይዘምራል ...ዛሬም ይፎክራል ?
ሰላም ነው ጠጠሩ .... ሰላም ናት ወንጭፉ?
እዛስ አቅል ገዛ ጎሊያድ ተራራው ጎሊያድ ግዙፉ?

እልፍ አላፍ ጎሊያድ ከቦን ሲደነፋ
ወንጭፉን ጠቅልሎ ምነው ዳዊት ጠፋ ?
ብሎሃል በልልኝ!!

ለረከሰ ጠጠር ለሞላ ወርዋሪ
‹‹ወንጭፍህን ስጠው ለዚህ ታሪክ አውሪ››
ብለህ እዘዝልን!!

እንዴት ነህ ጌታ ሆይ... ሰማይ ቤት እንዴት ነው?

የሙሴ አልጋ ወራሽ እያሱ ሰላም ነው....
ያቆማትን ፀሃይ ግቢ ቢላት ምነው...
ያው እንደምታውቀው
አስራ ሶስት ወራት ነው ፀሃይ የምንሞቀው...
ኧረ ፀሃይ በዛ
ኧረ ፀሃይ በዛ
ኧረ ፀሃይ በዛ
የመጣው ወር ሀሉ ፀሃይ እያዘለ
የተሸመው ሁሉ ‹ፀሃይ ነኝ› እያለ
የአስራ ሶስት ወር የግዜር ፀሃይ
የአስራ ሶስት ወር የሰው ጀምበር
ባቃጠላት ምድጃ አገር
ምን ታምር ሊኖር ይችላል ፀሃይ ሁኖ እንደመፈጠር....

ኧረ እግዜር በናትህ....
ኧረ እግዜር በናትህ...በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!

እናልህ እግዜር ሆይ ማጣፊያው አጥሮናል
ስም ያለው ሞኝ ነው ሁሉም ይጠራናል...
ጳውሎስ ሲሉን ...አቤት
ጴጥሮስ ሲሉን ...ወይየ
ይሁዳ ሲሉንም አቤት እንላለን
ስማችንን ሸጠን ...ሰላሳ ጭብጨባ እንቀበላለን

ተወው የኛን ነገር ...ሰማይ ቤት እንዴት ነው ....
ሂዋንስ ደህና ናት?
ያው የልጅ ልጆቿ
በእግሯ ተተክተው
የፍሬው ሲገርምህ
ግንዱንም አንክተው
ለፍጥረተ አዳም
ባይኑ ያገምጡታል
ሰይጣንም ደህና ነው
ኑሮ ተስማምቶታል....
ሰውን ለማሳሳት
ላይ ታች ማለት ትቷል
ሳይጠራው የሚጎርፍ ህዝብ በዝቶለታል...!

ኧረ እግዜር በናትህ በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!!

Sunday, August 3, 2014

እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ

ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር
እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ
ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤
በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ ፤
ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ
እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን
የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ፡፡
ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት
በማይቻል ዕንቊ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡
መልክአ ማርያም
ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ
እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና ዕርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ ዐበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡
እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽዕ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡
እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ መድኃኔዓለምን በማህጸንዋ ጸንሳ ዘተኝ ወር ፤ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡
ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር /መዝ 136¸8/ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሎአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡ የዜማም ጊዜ ደረሰ የቀረ… ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ” ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ /መኃ 2¸1ዐ-13/
ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን መከራ ስድት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18¸4/
የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ /መዝ 14¸13/ የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን ዐረፈች፡፡
እመቤታችን ጥር 21 ቀን ዕረፍት በሆነበት ዕለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ ዕረፍት /የመቃብር ቦታ/ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል፡፡ እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች ፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ /መዝ 44¸9/
ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ” ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/ ሰጥታው ዐረገች፡፡
እመቤታችን ለቶማስ ሰበን /መግነዟን/ ሰጥታው ዐረገች
ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን;” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን /መግነዟን/ ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡
ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ /ረዳት/ ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ /ዋና/ ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡
ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና ዕርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጻመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡
የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ /በጾመ ፍልሰታ/ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡
ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች ዕመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን ፤ ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ጾመ መድኃኒት ያድርግልን- አሜን ፡፡

Thursday, July 31, 2014

ከዲ/ን መስፍን ደበበ
እርሱ እናቴ እኔን ቅሪት እያማጠኝ፤
በልጅነት ሊገላገል በሐሳብ ያረገዘኝ፤
በማኅፀን ሰፋድሉ በትምህርቱ እኔን ስሎ፤
በመዶሻው እኔን ጠርቦ አስተካክሎ፤
እጄን ይዘህ አለማምደህ እንዲያ ስድህ፤
ቃለ ነገር ቃለ ምሥጢር እየጋትህ፤
ጠንካራውን ጥሬ ቃሉን አስቆርጥመህ፤
አንተ አብይ ባሕር የትምህርት ውቅያኖስ፤
ምርጥ ዕቃ ማዕዘን ዕብነ አድማስ፤
በእንቁላል ቅርፊት ቀድቼ የረካሁኝ ከአንደበትህ፤
ርዕሰ እውቀት አንተ አፈ ዝናም በትምህርትህ፡፡
አሕዛበ-ምድር ማንነቴን በጠብታህ ጎበኘሃት፤
የነፍሴን እርሻ አጥግበህ በልምላሜ ከደንካት፡፡
ሕሊናዬን በተመስጦ መንኮርኩር ስታከንፋት፤
ከታችኛው ከእንጡረጦስ ከበርባኖስ ስታጠልቃት፤
ዖፈ ጣጡስ መጥቀህ በረህ የነገርኸኝ፤
እንደ ሙሴ ከእግረ ታቦር ያላቆምኸኝ፤
አለማወቅ ጥቁር ካባ፤ የጨለማን መጋረጃን ያራቅህልኝ፤
ኢትትሃየድ እያለ ወራሴን ስታለምደኝ፤
ምሥጢሩን ስትቀዳ ዘቦቱን ስትነግረኝ፤
የሰብዕና ዘበኛዬ እኔን በትምህርቱ ንቅሳት ሲነትበኝ፤
ያኔ ነበር የነቀሰኝ በልቡናዬ ሕያው ቃሉን የከተበኝ፤
በጉልጓሎ በእርሻው ቦታ የጠመደኝ፤
እያረሰ ጅራፍ ቃሉን ጆሮዬ ላይ ሲያጮህብኝ፤
ከሃያው ክንድ ከመቅደሱ ከሚፈልቀው፤
ከዙፋኑ ከቃል ሥግው ከሚፈሰው፤
እንደ መስኖ ሊቀላቀል ከሚወርደው፤
ከእኔ ሕይወት ከሸለቆ ከአዘቅቱ ሲንዶሎዶል፤
የመብል ዛፍ ፍሬ በኩር ሲያበቅል፤
ያኔ ነበር ስሜ ሽቶ ከጌታ ስም ሲቀላቀል፤
ሃይማኖት የፍቅር እሳት ሲንቀለቀል፤
ተቆጠርኩኝ ግብር ገባሁ ከቤተ ወንጌል፡፡

Sunday, July 27, 2014

ጾም



==> ~ † ~ “ጾም ትፌውሥ ቁስለ ነፍስ ወታፀምም ዂሎ ዘሥጋ ፍትወታት
ትሜሕሮሙ ጽሙና ለወራዙት።”~ † ~ <==

==> “መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም’’ ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፰ (8፥8) ለዚህ ነው ደንኤልም በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። ያለው ት/ዳን. ፲፥፪-፫ (10፥2-3) ያለም መድሃኒት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንኑ ሲያስረግጥ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል በማለት በማቴ. ፬፥፬ (4፡4)

==> በት/ኢዩ. ፪፥፲፪-፲፫ (2፡12-13) አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።

==> ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ። ት/ኢዩ.፩፥፲፬ (1፥14)

==> ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ማለት ነው፡፡ ወይም ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጉመዠውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ዳዊት በመዝ.108፥25 ላይ ሰውነቴ በፆም ደከሙ ጉለበቴም ቅቤን በማጣት ከሳ ያለው፡፡ ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና አለው፡፡

==> ከጥንት ከበሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የበሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውኃ ባፋቸው አይገባም ነበር። ዘጸ.34፥28።
በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰውና ቁጣው የሚበርደው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር። ዮና 3፥5-10
==> በአዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መደኃኒታችን ኢየሰሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው። ማቴ.4፣2፤ ሉቃ.4፣2 ፡፡ በዚህም በስስት፣በፍቅረ ነዋይና በትዕቢት የሚመጣብንን ጠላት ዲያብሎስን በጾም ድል እንደምናደርገው አሳይቶናል። ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር ርኩስ መንፈስ በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ማቴ.17፥21፤ማር. 9፥2። በመሆኑም ጾም ለእኛ ታላቅ ጸጋና ኃይላችን ነው፡፡
==> ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እያሉ ነበር። የሐዋ.13፥2፡፡ ይህም የሚያመለክተው ጾምና ጸሎት የማይነጣጠሉ መሆናቸውና ጾምን ከጸሎት ጋር ስናስተባብር መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀርበን ነው፡፡ በጾም የተዋረደ እና ለጸሎት የተጋ ሰውነት ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ የተዘጋጀ በመሆኑ እግዚአብሔር ያዝዘናል እኛም እንታዘዛለን።

==> የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ ከኃጢአት ቁራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ለአምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን ሥጋንና ቅቤን ወተትና ዕንቁላልን ማራቅ ታዟል፡፡ባልና ሚስትም በአንድ ምንጣፍ አይተኙም፡1ቆሮ.6፣5፡፡ ‘ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ነዑድ ነው፣ክቡር ነው፡፡’’ እንደተባለ ጾመኛው ለምሳው ወይም ለእራቱ ያለወን ወጪ ነዳያንን እንዲረዳበት ለደኩማን ድርጅት ቢሰጥ ወይም በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን ቢመጸውት ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡
==> ጾም የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ ከኃጢያት ለመንጻት ስለራስ የታሰበውን ለነዳያን በመስጠት የሚጾም መሆኑን መረዳት አለብን ፡፡ ጾም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ነው፡፡ በዲዲስቅልያ 1፡5 ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው ተብሏል፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዙትን በስደትና በምርኮ ያሉትንም በጾም ወራት ማስታወስና ስለ እነርሱ መጸለይ ይገባል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ክፉ ከማየት ክፉ ከመናገር እና ክፉ ከመስማትም ጥምር መጾም እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

ስለዚህ በዚህች በተቀደስች ወርሐ ነሐሴ ጾመ ፍስለታ ከመጾማችንና ቤተክርስቲያን ሄደን ከማስቀደሳችን ጋር አብሮ ጎን ለጎን መደረገት ያለበትንም በማለመርስታ የተቸገሩትን በመርዳት መልካምና አርአያ የሆነ ተግባር በማድረግ እንዲሆን በማለት መልካም የበረከት ጾም እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፡፡