Sunday, July 27, 2014

በገና

አሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ !!! መዝ.፻፵፫፥፱

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ መሰረት ሶስት ዓይነት የዜማ ዓይነቶች አሉ

እነሱም ግዕዝ እዝል እና አራራይ ናቸው ፡፡

እነዚህ ዜማዎች ከሚዜሙባቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ በገና ነው ንጉሥ ዳዊት በበገና ደርዳሪነቱ እጅግ የተመሰገነ ነበረ “ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር ። ” ፪ሳሙ. ፮፥፭ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደምናገኘው በገናን የሚደረድሩ ከሌዊ ወገን እንዲሆኑ ያደረገውም ቅዱስ ዳዊት ነው “ ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ ። ” ፩ዜና. ፲፭፥፲፮ እስራኤላውያን ግን በገናን በመተዋወቅ ከዓለም ቀዳሚ ሕዝቦች ናቸው ፡፡ በእስራኤላውያን ዘንድ በገናን የሚደረድሩ የተለየ ክብር እና ቦታ እንደ ነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ፡፡ “ የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ ። ” ዘፍ. ፬፥፳፩

በገና ለእግዚአብሔር ማመስገኛነት እንዲውል እና በገና የሚደረድሩትም በቅዱሳት በዓላት ላይ በተለየ ቦታ እንዲቆሙ ሥርዓት የሰራው ቅዱስ ዳዊት ነው “ ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ ። ፪ዜና. ፳፱፥፳፬‐፳፮
በገናን በመደርደር እና እግዚአብሔርን በማመስግን ከርኲስ መንፈስ ከደዌ መፈወስ ይቻላል “ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው የሳኦልም ባሪያዎች እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት ። ሳኦልም ባሪያዎቹን መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው ። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ እነሆ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው በነገርም ብልህ መልኩም ያማረ ነው እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ ። ” ፩ሳሙ. ፲፬፥፲፮‐፲፰

በእስራኤላውያንም ሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በገና ለጸሎት ማቅረቢያ እንጠቀምበታለን በተላይ ወደ ተመስጦ በመውሰድ በእንቃእዶ ልቦና ጸሎትን ወደ እግዚአብሔር ለማደረስ በገናን የሚያክል መሳሪያ የለም “ እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው ልዑል ሆይ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ በማለዳ ምሕረትን በሌሊትም እውነትህን ማውራት አሥር አውታር ባለው በበገና ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ ። ” መዝ. ፺፩፥፫
በጥንተ እስራኤላውያን ታሪክ በገናንን ለአዋጅ ማስነገሪያነት እና ለደስታ መግለጫነት ይጠቀሙበት ነበር “ አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ የመለከትንና የእንቢልታን የመሰንቆንና የክራርን የበገናንና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል ። ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ። ” ዳን. ፫፥፬‐፮

እስራኤላውያን ልዑል እግዚአብሔር አምላክ ከፈተና ባዳናቸው ከአደጋ ሲታደጋቸው እግዚአብሔርን በበገና ያመሰግኑ ነበር “ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ ። በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ ። ” ፪ዜና. ፳፥፳፯‐፳፰
በገናን የሚደረድሩ ሌዋውያን ካህናት መስዋዕተ ኦሪት ሲያቀርቡ አብረው በበገና እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር “ መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በመሥራቅ በኩል ቆመው ነበር ። ” ፪ዜና ፭፥፲፪

እስራኤላውያን በሚያደርጓቸው ትልልቅ ግብዣዎች ወይም የልደት በዓላቸው ላይ በገናን በመደርደር የታወቁ ነበሩ “ መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም እጁም ያደረገችውን አላስተዋሉም ። ” ኢሳ. ፭፥፲፪

ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ወደ ሰማያት በተነጠቀ ከሰማቸው የምስጋና ድምፆች አንዱ የበገና ድምፅ ነበር “ እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ ። ” ራእ. ፲፬፥፪ በተመሳሳይ መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ ቅዱሳት መላእክት እግዚአብሔርን በበገና እንደሚያመሰግኑ እንዲህ ሲል ገልፆታል “ መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው ። መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ ። ” ራእ. ፭፥፰

በዓለም የረጅም እድሜ ባለ ፀጋ የመዝሙር መሳሪያ የሆነው በገና በኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ በእድሜው አቻ የለውም ፡፡ በገና በእጅ ከሚከረከሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ሲሆን የሚሰራው ከእንጨት እና ከእንስሳት ተዋፅኦ ነው ፡፡ ሳጥኑ አምዶቹ በርኩማው ከእንጨት ሲሰሩ አውታሮቹ ደግሞ ከከብት ጅማት ወይም ከከብት አንጀት ይሰራሉ ፡፡ የበገናዎች አውታሮች ቁጠር አስር እንዲሆን የተደረገው መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ነው “ እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት ። ” መዝ. ፴፪፥፪ የድሮ በገናዎች ሳጥኑ በክብት ቆዳ ሲሸፈን አሁን አሁን ደግሞ በእንጨት ውጤት ይሸፈናል ፡፡ በገና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን የተለያዩ የኢትዮጵያ ነገሥታት በገና ይደረድሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግት ያስረዳሉ ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስ እና አፄ ምኒልክ በገና ይደረድሩ ነበር ፡፡ በዚህ ዘመን በተለይ በገናንን በሚገርም የአደራደር ስልት በመደርደር በዓለም ዘንድ በሚገባ በማስተዋወቅ እንዲሁም በገናን ጠብቀው ካቆዩን መካከል ባለ ውለተኞቻችን መካከል እጅግ የማደንቃቸው መጋቢ ስብሐት ዓለሙ አጋ በጣም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ፡፡

የበገና ምሳሌዎች

በገና የእመቤታችን ምሳሌ ነው ፡፡

የሚያወጣው ድምፅ ደግሞ በእመቤታችንን ጣዕም እና ፍቅር ይመሰላል ፡፡
አስሩ አውታር በአስሩ ቃላተ ኦሪት ይመሰላል
በቀኝ እና በግራ ያሉት ሁለቱ አምዶች ደግሞ በቀኝ ያለው በፍቅረ እግዚአብሔር ሲመሰል በግራ ያለው አምድ ደግሞ በፍቅረ ቢጽ ይመሰላሉ ፡፡
በሌላ መልኩ በግራ ያለው አምድ የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ሲሆን በቀኝ ያለው አምድ ደግሞ ሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ነው ፡፡
ከእንጨት መሰራቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት መሰቀሉን ያመለክታል ፡፡
በገና ይህን ያህል ታሪክ ያለው ንዋየ ቅዱሳት ቢሆንም አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው እንደውም ከጥቂት አመታት በፊት ወደ መጥፋቱ ተቃርቦ ነበር ከተወሰኑ አመታት ወዲህ ግን በርካታ ወጣቶች በገናን ሲደረድሩ መመልከት እየቻልን ነው ለዚህ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን የበገና ድርደራ ትምህርት ክፍል በመክፈት ኦርቶዶክሳውያን እንዲማሩ እያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ የበገናንን የመጥፋት ስጋት በተወሰነ መልኩ ታድጓል ይህ መልካም እና የተቀደሰ ጥረት ግን በሁሉም አካላት ሊታገዝ ይገበዋል ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ላደረገው መልካም ስራ ሊመሰገን ይገባዋል ፡፡ እኛም በገናን መደርደር በመማር እግዚአብሔርን እናመስግን ይህንን ድንቅ የእግዚአብሔር ማመስገኛ ቅዱስ እቃ ለተተኪ ትውልድ እናስተላልፍ !!!

“ እግዚአብሔርን በመለከት ድምፅ አመስግኑት በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት ። ” መዝ. ፻፭፥፫

“ እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው ልዑል ሆይ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ በማለዳ ምሕረትን በሌሊትም እውነትህን ማውራት አሥር አውታር ባለው በበገና ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ ። ” መዝ. ፺፩፥፫

“ እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት ። ” መዝ. ፴፪፥፪

No comments:

Post a Comment