Sunday, July 27, 2014

ክርስቲያናዊ አለባበስ

ክርስቲያናዊ አለባበስ

“ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ወንድም የሴትን ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፡፡” ዘዳ. 22፡5

ስለ አለባበሳችን እንወያያለን ዛሬም እህቶቻችን ላይ እናተኩራለን አበዛኸው ምነው እኛን ብቻ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለው፡፡

ስለ አለባበስ መነጋገር ያስፈለገን እውነተኛ ክርስቲያን በአነጋገሩ፣ በአረማመዱ፣ በአመጋገቡ፣ በአለባበሱ፣ ብቻ በሁሉ ነገሩ የተለየ መሆን ስላለበት ነው ይኸውም ሁሉን በአግባብና በሥርዓት ስለማድረግ ነው እህቶቻችን ላይ ማተኮር ያስፈለገው ደግሞ በአብዛኛው በዚህ ረገድ ትችት የሚበዛው እነሱ ላይ ስለሆነ ነው፡፡

እነሆ ውድድሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረና እየከፋ ነው ለመልካም ነገር መወዳደር ባልከፋ ነገር ግን በከተማችን በተለይም በዋና ዋና መንገዶች ላይ የምናየው የእህቶቻችን አለባበስ አንዷ ከሌላዋ ልቃና በልጣ ለመታየት የሚደረግ ግብግብ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ በእርግጥ እህቶቻችን በዚህ እንደማይስማሙ እናውቃለን አብዛኞቹም ስለተመቸኝና የምወደው አይነት አለባበስ ስለሆነ ነው እንዲህ የምለብሰው ይሉናል ይሁን እንጂ እውነታው ሌላ ይመስላል ምክንያቱም:-
* ብርድልብስ ለብሰን እንኳን በማንቋቋመው የብርድ ወቅት ሰውነትን በቅጡ የማይሸፍን ብጣሽ ጨርቅ ጣል አድርጎ መውጣት እንዴት ያለ ምቾት ነው?

*እጅግ አስጨናቂ ሙቀት ባለበት ሰዓት ሰውነት ላይ ተጣብቆ ሌላ ጭንቀት የሚፈጥር አለባበስ እንደምን ብሎ ያስደስታል?

ዓላማችን ምንም ይሁን እሱ ላይ የመከራከር ፍላጎት የለንም ነገር ግን አለባበሳችንን እንደ ክርስቲያን እንፈትሸው ዘንድ ይገባልና ይህ ተፃፈ

መሰልጠን ወይስ መሰይጠን?

አብዛኞቹ ሴቶች ይህን ተግባር ስልጣኔ እንጂ ስህተት ነው ብለው አያምኑም፡፡ ለነዚህ ሴቶች ከኃይማኖት ብቻ ሳይሆን ከባህላችን ጭምር ያፈነገጠውን የምዕራባውያን አለባበስ መልበስ ዘመናዊነት ነው፡፡ ላንቺስ? መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል?
-----------------------------------------/////////////////////////------------------------------------

ማንኛዋም ሴት የሰውነቷን ቅርፅ የሚያሳይ ወይም ክፍትፍት ልብስ ለብሳ መሄዷ የሁሉንም ወንዶች ስሜት መፈታተኗ እርግጥ ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ህይወት ደካማ የሆኑትን ደግሞ ለኃጢያት አጋልጦ ይሰጣል፡፡ እዚህ ላይ የተሳሳተው በራሱ ደካማነት ነው ብሎ ምክንያት መስጠት አይቻልም እግዚአብሔር የሚጠይቀው በማን ተሰናከለ የሚለውን ጭምር ነውና በክርስትና ደግሞ ሰውን ማሰናከል እጅግ የከፋ ኃጢያት ነው፡-

“ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባህር መስጠም ይሻለው ነበር፡፡” ማቴ. 18፡6

አንዳንድ ሴቶች እግዚአብሔር ምን ሰራሽ እንጂ ምን ለበስሽ አይለኝም ይላሉ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል

“እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለው፡፡” ትን.ሶፎ. 1፡18

እንግዲህ የሴቶቹን እንቀበል ወይስ የእግዚአብሔርን ምርጫው ያንቺው ነው እህቴ መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል፡- “ከስው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡” የሐዋ. 5፡29

በሴቶችና በወንዶች መካከል የአለባበስ ልዩነት ሊኖር ይገባል

“ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ወንድም የሴትን ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፡፡” ዘዳ. 22፡5

ታዲያ ቀሚስን የወንድ ሱሪን የሴት ማን አደረገው? ይህ የሰነፍና ለስህተታቸው ምክንያትን የሚሹ ሴቶች የሚያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ኦርቶዶክሳውያን የእግዚአብሔርን ቃል አውቀን ልንፈፅመው እንጂ በቃሉ ላይ የምንፍቅና ጥያቄ እናነሳ ዘንድ ተገቢ አይደለም ግን ደግሞ ተፈጥሯችንን ብቻ በማየት ህሊናችን እራሱ ቢናገር ሱሪ የሴት ነውን? ቀሚስስ የወንድ ነው እንዴ “ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁምን? 1ኛ ቆሮ. 11፡14

“ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም፡፡” 1ኛ. ቆሮ. 11፡16

ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ስህተት መሆኑን መናገር እንጂ መከራከር አያስፈልግም ክርስትና በምርጫ ነውና፡፡

“በፊትህ እሳትና ውሃን አኑሬአለው ወደ ወደድከው እጅህ ክተት፡፡” ሲራ. 15፡15

እዚህ ላይ ግን ቀሚስ ሲባል ከውስጥ ሱሪ የማይሻለውን ብጣሽ ጨርቅ እንዲሁም ቁመቱ ረዥም ሆኖ ከሰውነት ጋር የሚጣበቀውን አይነት አለባበስ ማለት እንዳልሆነ ልብ እንበል፡፡

እህቶቻችን ሆይ ማስተዋልን ትላበሱ ዘንድ እንለምናችኋለን መሰልጠንና መሰይጠንም ትለዩ ዘንድ ይሁን ሰውነትሽ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነውና ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጊለት፡፡

ደግሞም ክርስትና ራስ ወዳድነትን አብዝታ ትጠላለች ምንም ነገር ስናደርግ ስለ ሌላው ሰው ልናስብ ያስፈልገናል እኛስ ሰውን ወደ ዝሙት ሊያመራው ስለሚችል አለባበሳችን እጅግ ተጨነቅን ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ ወንድማችንን ስለማሰናከል ምን አለ

“መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም፡፡” 1ኛ.ቆሮ 8፡13

እንግዲህ ክርስትና እዚህ ድረስ ነው ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለ ወንድሞችና እህቶቻችን የምናስብባት ለእነሱም መሰናከያ እንዳንሆን እየተጠነቀቅን ሁሉን በአግባብና በሥርዓት የምናደርግባት፤ እምነታችንን በምግባር የምንገልጽባት ናት፡፡

“በእውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን፡፡ ትን.ኤር. 13፡27

እህቴ ሆይ አንቺም ኤርሚያስ እንዳለው ኢትዮጵያዊነትሽን ጠብቂ የምዕራባውያን በዓል ከሆነው አለባበስም ሆነ የምንዝር ጌጥ ራስሽን አርቀሽ በሚያኮራው ኢትየጵያዊ ባህላችን ትዋቢ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳሽ፡፡

ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡ አሜን!!!!

ሁላችን ምግባር ያለው እምነት እንዲኖረን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን!!!

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ!!!

1 comment:

  1. ተባረክ ወንድሜ ጥሩ ትምህርት ነው ጌታ ይባርክህ

    ReplyDelete