Sunday, July 27, 2014

ጴጥሮስ ወጳውሎስ ወቅዱስ ዮሐንስ ዘንስር

ጴጥሮስ ወጳውሎስ

ቅዱስ ጴጥሮስ

ጴጥሮስ ማለት ዓለት ማለት ነው፡፡ ማቴ. 16፥18 በዕብራይስጥ ኬፋ ይለዋል፡፡ የመጀመሪያ ስሙ ስምዖን ነው፤ ትውልዱም ከነገደ ሮቤል ነው፡፡ አባቱ ዮና ይባላል፡፡ የተወለደው በገሊላ አውራጃ በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ጴርቴዋ የምትባል ሚስት ነበረችው የሚተዳደረው ዓሣ በማጥመድ ነበር፡፡ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር ዓሣ ከሚያጠምድበት ተጠርቶ ሐዋርያ ሆኗል፡፡ ማቴ. 4፥19

ጴጥሮስ የዋህ፣ ፈጣን ቁጡ ነበር፡፡ የዋህነቱ ጌታ በባሕር ላይ ሲሄድ አይቶ ጌታ አንተስ ከሆንክ ወደ አንተ እንድመጣ አሰናብተኝ ብሎ በባሕር ላይ ሲሄድ በመሞከሩ ማቴ. 6፥45፣ ፈጣንነቱ ጌታ ደቀመዛሙርቱን በቂሣርያ ሰዎች ማን ይሉኛል ብሎ ጠይቋቸው ሙሴ ነው፣ ኤልያስ ነው ይሉሃል ባሉትና እርሱም መልሶ እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ጴጥሮስ ፈጥኖ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ ብሎ በመመለሱ ማቴ. 16፥16 ቁጡነቱም አይሁድ ጌታን በያዙት ጊዜ ተቆጥቶ የማልኮስን ጆሮ በሰይፍ በመቁረጡ ዮሐ. 18፥10 ላይ ያስረዳል፡፡ መዋዕለ ስብከቱ 50 ዓመት ነው፡፡ /ገድ ሐዋ፣ ዜና ሐዋ/

ንጉሡ ኔሮን ቄሣር መምለኬ ጣዖት ነበረና በሃይማኖት ምክንያት አስሮት ነበር፡፡ አካይያ ዘምቶ ጠላቱን ድል ነሥቶ ሲመለስ ለጣዖት ስገድ ቢለው አልሰግድም አለ፡፡ በችንካር ተቸንክሮ በመስቀል ተሰቅሎ ይሙት ብሎ ፈረደበት ከዚህ በፊት አሕዛብ ሊጣሉት ሲነሱ ወደ ጌታ ሲያመለክት እሳት ከሰማይ ወርዳ ታጠፋለት ነበር አሁንም እሳት ከሰማይ ወርዳ ትብላቸው ብሎ ወደ ጌታ ቢያመለክት ጌታ በመስቀል ተሰቅሎ ታየው ዳግመኛ በሮም ሰቀሉህን? አለ አንተ ብትፈራ እንጂ ነዋ አለው፡፡ ፈቃድህስ ከሆነ ብሎ እንደ ጌታዬ አቁማችሁ ሳይሆን ቁልቁል ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ አላቸው በራሱ ዘቅዝቀው ሰቅለውታል፡፡ ዕረፍቱ በዚህች ሐምሌ 5 ቀን ይታሰባል፡፡ ሥጋውንም ደቀመዝሙሩ መርቄሎስ ከመስቀሉ አውርዶ በወተት በወይን አጥቦ ሽቶ ቀብቶ በነጭ ሐር ገንዞ እንዳይፈርስ በማር በተመላ ሣጥን አድርጎ ቀብሮታል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ

ጳውሎስ ማለት ንዋይ ኅሩይ (የተመረጠ ዕቃ) ማለት ነው፡፡ ሐዋ.9፥15 አንድም ብርሃን ማለት ነው፡፡ አንድም መድቅሕ ማለት ነው፡፡ ድንጋይ በመዶሻ ተጠርቦ ለሕንፃ ሥራ እንዲውል አሕዛብም በእርሱ ትምህርት ታንፀው ለገቢረ ጽድቅ ይበቃሉና የመጀመሪያ ስሙ ሳውል ነው፤ ሳውልም ማለት ጸጋ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ማለት ነው፡፡ ፊል. 3፥5 አባቱ ዮስአል ይባላል፡፡ የተወለደው ጌታ በተወለደ በ5 ዓመት በጠርሴስ ነው፡፡ ከ15 ዓመቱ ጀምሮ ኢየሩሳሌም በታላቅ እኅቱ ጌት ተቀምጦ ከመምህር ገማልያል ሕገ ኦሪትን መጻሕፍተ ነቢያትን ሲማር አድጓል፡፡ ሐዋ. 22፥3 ለሕገ ኦሪት ቀናዒ ከመሆኑ የተነሣ ክርስቶስን ዕሩቅ ብእሲ ወንጌልን ዲቃላ ሕግ እያለ ሐዋርያትን ይቃወም ምእመናንን ያሳድድ ነበር፡፡ በወንጌል ያመነው ጌታ በዐረገ በ8ኛ ዓመት ነው፡፡ ምዕመናንን ለማሳደድ ከሊቀ ካህናት የሹመት ደብዳቤ ተቀብሎ ወደ ደማስቆ ሲሄድ መብረቅ ጣለበት፤ ደንግጦ ወደቀ ወዲያውም ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ አንተ ማነህ አለ ምእመናንን ከዋሉበት አላሳድር ካደሩበት አላውል የምትልብኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፣ ሰይፍ ቢረግጡት የረገጠው ሰው እንጂ ሰይፉ ይጎዳልን፣ አንተስ እኔን ብትክድ ምእመናንን ብታሳድድ አንተ እንጂ እኔ እጎዳለሁን አለው፡፡ አሁን ምን ላድርግ አለው ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባ የምታደርገውን ይነግሩሃል አለው፡፡ ከእርሱ ጋር የነበሩም ድምጹን ይሰማሉ መልኩን ግን አላዩም፤ ከወደቀበት ተነሥቶ ዓይኑ ጠፍቷልና ሰዎች እየመሩት ቤተ ይሁዳ አደረሱት እኅል ውኃ ሳይቀምስ 3 ቀን ውሎ አድሯል፡፡

ከ72 ቱ አርድዕት አንዱ ሐናንያ በደማስቆ ይኖር ነበር ጌታ በራዕይ ታይቶት ጳውሎስን አሳምነህ አጥምቀው አለው፡፡ ምርጥ ዕቃ አድርጌዋለሁና ሂድ ይቀበልሃል አለው፡፡ ሄዶ ወንድሜ ሳውል በመንገድ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ያድርብህ ዘንድ ወዳንተ ልኮኛል ብሎ ቢዳስሰው ዓይኑን ሸፍኖት የነበረው እንደ ቅርፊት ተቀርፎ ወድቆለታል፡፡ ሐዋ. 9፥1-19

በ69 ዓ.ም ሮም ገብቶ ሲያስተምር ንጉሡ ኔሮን ቄሣር አሥሮት ነበርና አካይያ ዘምቶ ጠላት ድል ነሥቶ ሲመለስ ጥሩት አለ፤ መስቀሉን በእጁ ይዞ ቀረበ፤ ተቆጥቶ በሰይፍ ቅጡት አለ፤ እንደ በግ እየነዱ ሲወስዱት የንጉሡ ልጅ አገኘቻቸው፤ አምና ነበርና መጎናጸፊያሽን ስጪኝ አላት ሰጠችው በዚያ ሸፋፍነው ሰይፈውታል፡፡ ደሙም ሰማየ ሰማያት ወጥቶ ቀተሉኒ በዓመጻ እያለ ተካሷቸዋል፡፡ ‹‹ደምከ ጴጥሮስ ወልደዮና በጽዋዐ መስቀል ተቀድሐ፤ ወደመ ጳውሎስ ሰማያተ ጸርሐ›› እንዳለ ደራሲ እሱን ገድለው ሲመለሱ የንጉሥ ልጅ አገኘቻቸው ጳውሎስስ? አለቻቸው፡፡ በልብስሽ ሸፋፍነን በሰይፍ ገደልነው አሏት፡፡ ልብሴን መልሶልኝ ከጴጥሮስ ጋር አሁን በዚህ ሲያልፍ እያየሁት ገደልነው ትሉኛላችሁን አለቻቸው ልብሷን አይተው አምነዋል፡፡ ተቆርጦ የወደቀ ራሱንም ከአንገቱ ቢያጋጥሙት እንደ ቀድሞው ሆኖላቸው ቀብረውታል፡፡ ዕረፍቱ በዚች ሐምሌ 5 ይታሰባል፡፡

የእኚህ ቅዱሳን አባቶች ጸሎታቸው በረከታቸው ከሁላችን ጋር ይኑር፡፡



                                                ቅዱስ ዮሐንስ ዘንስር

ከ 12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ አባቱ ዘብዲዎስ እናቱ ማርያም ባዎፍሊያ ይባላሉ የሐዋርያው የዕቆብ ወንድም ነው፡፡ ከአባቱና ከወንድሙ ጋር ዓሳ በማጥመድ ላይ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያነት መረጠው፡፡ እሱም ሁሉን ትቶ ተከተለው፡፡
በወንጌል ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር/ተብሎ ስልተጠቀሰ /የጌታ ወዳጅ ፡/ፍቁረ እግዘእ ይባላል፡፡ መድሃኒታችንም ወልደ ነጎድጏድ ብሎ ሰይሞታል፡፡ በስሙ የሚጠራውን ወጌል በመጻፉ ከ አራቱ ወንጌላውያን አንዱ ነው፡፡

ከሌሎች ወንጌላውያን ይልቅ ምስጢረ ሥላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን አምልቶ አስፍቶ በመጻፉ ታኦሎጎስ ነባቤ መለኮት ተብሎ ይጠራል፡፡

ዚያች በመከራ ሰአት በጌቴሰማኒ በአትክልት ቦታ እስከ ቀራኒ ኮረብታ ባለመለየቱ ፍጹም ሆነ ፍቅሩን አስመስክሯል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ቤተክርስቲያንን በመወከል በእግረ መስቀሉ ስር ተገኝቶ ቅድስት ድንግል ማርያምን ከመድሃኒታችን ለዓለም ሁሉ በእናትነት አደራ የተቀበለ ታላቅ አባት ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ዙፋን ከሚሸከሙት ከአራቱ እንስሳ ከኪሩቤል መካከል በገጸ ንስር ይመሰላል ንስር በአየር እየበረረ ቁልቁል በተመለከተ ጊዜ በምድር ላይ የሚኖር ቅንጣት ሥጋ እንደሚመስል ቅዱስ ዮሐንስም አካል ከህልውና ተገልጾለት ንጽሃ ሥጋ ንጽሃ ነፍስ ንጽሃ ልቦና ተሰጥቶት በመጀመሪያ ቃል ነበረ ብሎ ጽፏል በሶስቱ መልእክቶቹም ስለ መንፈሳዊ ፍቅር በስፋት ገልጽዋል፡፡ በፍትሞ ደሴት በግዞት በነበረበት ወቅት የተገለጸለት አስደናቂ ራዕይ የዮሐንስ ራዕይ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ የበአሉም መታሰቢያ ጥር 4 ቀን በየዓመቱ ይከበራል፡፡

+++ ከወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ የፍቅር አባትና ሐዋርያ ረድኤት በረከት ይክፈለን +++
ሰባኬ ወንጌል መጋቤ ሐይማኖት ለቤተክርስቲያን ዘይደምፅ ቀርን
ነባቤ ለቤተክርስቲያን ዮሐንስ ፀሐያ ለኢትዮዽያ አምደ ብርሃን ዘፍጥሞ
መልአክ ዘበምድር መልአክ

ቅዱስ ዮሐንስ ሰባኬ ወንጌል መጋቤ ሐይማኖት ለቤተክርስቲያንም የሚመሰክር መለከት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፀሐይ በፍጥሞ ያለ የብርሃንም ምሰሶ በምድር ላይም ያለ መልአክ ነው፡፡

††
ዮሐንስ ማለት ፍሰሓ ወሐሴት ሠላም ርህራሄ ወሳህል ማለት ነው።

ወልደ ነጎድጓድ፣

አቡቀለምሲስ፣

ነባቤ መለኮት፣

ታዖሎጎስ ይለዋል፡፡

“ቃዳሚሁ ቃል ውእቱ” ብሎ ምስጢረ ሥላሴን አምልቶ አስፍቶ ይናገራልና፡፡

ፍቁረ እግዚእ ይለዋል፡፡ “ዝኩ ካልዕ ረድዕ ዘያፈቅሮ እግዚእ ኢየሱስ” ይለዋልና፡፡ ዮሐንስ 21፡7

መውደድንስ ሁሉንም ይወዳቸው የለምን ቢሉ የርሱ የተለየ ነውና፡፡

ከቶማስም የሱ መወደድ ይበልጣል፡፡

ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን ቢዳስሰው እጁ ከእሳት እንደገባ ጅማት ተኮማትሯል፡፡

እርሱን ግን በከናፍሩ ቢስመው በጭኑ ቢያስቀምጠው ምንም ምን አልሆነምና፡፡

ንጹህ ወድንግል ይለዋል፡፡ ጌታን ከመውደዱ የተነሳ ጌታም እናቱን እነዃት እናትህ ሲል

ድንግል ማርያምን በሱ በኩል ተሰታናለች፡፡ እኛም ዛሬ ልጆቿ ነንና ደስ ይበለን ይበላችሁ የድንግል ማርያም የአስራት፣ የተስፋና የስስት ልጆች፡፡ ዮሐንስ 19፡26፡፡

ዮሐንስ ሀገሩ ገሊላ አውራጃ ሲሆን ከታላቅ ወንድሙ ከያዕቆብና ከአባቱ ከዘብድዮስ ጋር ዓሣ እያጠመደ ይኖር ነበር። እናቱ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ስትሆን ማርያም ትባላለች።
†† ዮሐንስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን በሕይወትም በኑሮም ጌታ ስለሚመስል (ፍቁረ እግዚእ) ይባለል።

ነገረ መለኮትን በበለጠ ከሌሎች አምልቶ አስቶ በጥልቀት በማስተማሩ ነባቤ መለኮት (ታዖሎጎስ)ተሰኝቷል።

ስለጌታም ባለው ቅናት ባሳየው የሀይል ሥራ በኦኔርጌስ (ወልደ ነጎድጓድም) ተብሏል።

ፍጥሞ በምትባል ደሴት በራዕይ መጻእያትን በመግለጡ ባለራዕይ (በግሪክ አቡቀለምሲስ) ይባለል።

በዕለተ ዓርብ በመስቀል ሥር ተገኝቶ የጌታን መከራ መስቀል በማየቱ ፊቱ በሀዘን ስለተቋጠረ ቁጽረ ገጽ (ፊቱ በሀዘነ የተቋጠረ) ስምም ተሰቶታል።

ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የፋሲካን እራት ያዘጋጀ አንካሳን የፈወሰ ታለቅ ሐዋርያ ነው። (ሊቃስ 22፡8) እስከ መስቀል አምላኩን ተከትሎ እመቤታችንን በአደራ የተረከበ ባለአደራ ሐዋርያ ሲሆን ከጰራቅሊጦስ በዓል በኋላ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋራ በኢየሩሳሌም በአንጾኪያ በሎዶቅያ በእስያ ከተሞች በተለይ በኤፌሶን በአሁኑ ቱርክ አስተምሯል። (ዮሐ.19፡26)

በወጣትነት ዕድሜው ተጠርቶ በዕለተ ዓርብ የጌታን መከራ እያሰበ ያነባ የነበረ በፍቅር በታማኝነት እስከመጨረሻ ድረስ የጸና ከጌታ ያልተለየ ወንጌላዊ ሲሆን ወንጌልን ጨምሮ 3 መልዕክታትን የጻፈ እንዲሁም በበፍጥሞ ደሴት ራዕይ የጻፈ ታላቅ ሐዋርያ ነው።

†† መዋዕለ ስብከቱ 70 ዓመት ነው፡፡ መላ ዘመኑን ጌታ በዕለተ ዓርብ የተቀበለውን መከራ እያሰበ ቁጽረ ገጽ ሆኖ ሲያዝን ሲያለቅስ ኖሮ በዚህ ዕለት አርፏል፡፡ ይህም ሊታወቅ መላእክት መቃብሩን ቆፍረውለት ገብቶ ሲጸልይ ደቀመዝሙሩ ፋጊርን የኤፌሶንን ሰዎቸ በተማራችሁት ትምህርት ጸንታችሁ ኑሩ በላቸው ብሎ ላከው፡፡ ደርሶ ቢመለስ መቃብሩ አፈሩ ተመልሶ መጎናጸፊያውን መቋሚያውንና መነሳንሱን ከዳር አግኝቶታል፡፡ ሉቃስ 23፡26 2ቆሮ.7፡10

እግዚአብሔር አምላካችን ከሐዋርያው ወንጌላዊ ከቅዱስ ዮሐንስ ረድኤቱን በረከቱን ያሳድርብን፡፡

No comments:

Post a Comment