Sunday, July 27, 2014

ምክረ አበው

ምክረ አበው

“ልጆቼ! ሓኪሞች ብትሆኑ፣
መሀንዲሶች ብትሆኑ፣
የሽመና ሠራተኞች ብትሆኑ፣
መርከበኞችም ብትሆኑ መልካም ነው፡፡

ይህን ጥበብ መማራችሁም ጥሩ ነው፡፡

እኔ ግን ከዚህ የበለጠ ጥበብ አሳያችኋለሁ፡፡

በዚህ (በተማራችሁት ምድራዊ) ጥበባችሁም ሌላ ጥበብ ትማሩበት ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡

ሰማያዊን ጥበብ! ከላይ በገልጽኩላችሁና እናንተ በተማራችሁት ጥበብ ተጠቅማችሁ
ገንዘብ ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡ በዚህ ገንዘባችሁ ግን ድሆችን መርዳት ልመዱበት፡፡
ይህ የምነግራችሁን ጥበብ እንደ ቀላል የምታዩት አትሁኑ፡፡

መሀንዲሶች ብትሆኑ በምህንድስና ጥበባችሁና እውቀታችሁ በዚህ ምድር የሚያማምሩ ቪላ ቤቶችን ልትሠሩ ትችላላችሁ፡፡

በምነግራችሁ ጥበብ ግን
በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ የዘላለም ቤታችሁን ትሠራላችሁ፡፡

በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤታችሁ በጣም ብዙ ወጪ ብዙም ድካም ይጠይቃችኋል፡፡

በምነግራችሁ ጥበብ ግን ብዙ ልፋት የለውም፡፡

ወጪአችሁ መልካምና ፈቃደኛ መሆን ብቻ ነው፡፡

በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤት የተለያዩ ዓይነት ብረቶችና ማቅለጫዎች

እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን ትጠቀማላችሁ፡፡

በምነግራችሁ ጥበብ ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋችሁም፡፡

የሚያስፈልጋችሁ ብሎን ወይንም ብረት ወይንም የከበረ ድንጋይ ሳይሆን መልካም ምግባራችሁና በጎ ፈቃዳችሁ ብቻ ነው፡፡

እንደውም እኔ እነዚህ የተማራችኋቸው ጥበቦች ጥበብ ብዬ ለመጥራት በጣም እቸገራለሁ፡፡
ለምን ብትሉኝ ከምነግራችሁ ጥበብ ጋር ሳወዳድራቸው በጣም ስለሚያንሱብኝ አያያዛቸው ላላወቀበት ሰውም ብዙ ጉዳት ስለሚያመጡ፡፡

እስኪ አስተውሉት! አንድ ሰው በዚህ ምድር ባገኘው ጥበብና ገንዘብ ተጠቅሞ ድሆችን መርዳት ሲገባው አላግባብ ሲበላ ሲጠጣ በኋላ ግን በስኳር፣ በሪህ፣ በቁርጥማት፣ በራስ ምታት፣ በልብና በኩላሊት በሽታ የሚሰቃይ ከሆነ ይህ ጥበብ እለው ዘንድ እንዴት እደፍራለሁ? እንግዲያውስ ጥበባችሁ ጥበብ ይሁንላችሁ፡፡ ጥበባችሁ ለሥጋችሁም ለነፍሳችሁም የሚጠቅም እንጂ በዚህ ዓለምም ይሁን በሚመጣው ዓለም የሚጎዳችሁ አይሁን፡፡ ” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
2

No comments:

Post a Comment