Saturday, August 9, 2014

Why We Sometimes Write "Etc" In Exams?
Because It Means.
.
.
.
E-End Of
T-Thinking
C-Capacity

But Teacher Won't Ever Understand Our FEelings...

 

WHY STUDENT FAIL
Sundays-52 in a year,Days left 313
Summer holidays 50,Days left 263
8 hrs daily sleep-130 days GONe, Days left 141
1 hr daily playing means 15 days,Days left 126
2 hrs daily for eating means 30 days.Days left 96,
1 hr talking means 15 days.,Days left 81
Exams days 35 days,Days left 46
Eid & Gov holidays 20, Days left 26
Movies,TV at least 25 days,Days left 1
That 1 day is your BIRTHDAY.

 

Question by a student !!
If a single teacher can't
teach us all the subjects,
Then...
How could you expect a single student
to learn all subjects ?

 

Thursday, August 7, 2014

ንሥር BY DANIEL KIBRET

ንሥር እጅግ ግዙፍ ከሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡ ክብደቱ እስከ 6.7 ኪሎ ሲደርስ ቁመቱ ደግሞ ከአንዱ ክንፉ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ 2 ሜትር ተኩል ይደርሳል፡፡ በዓለም ላይ እስከ ስድሳ የሚደርሱ የንሥር ዝርያዎች ይገኛሉ፡

በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ንሥር የትንሣኤ ሙታን፣ አርቆ የማሰብ፣ ወደ ላይ የመምጠቅና የመነጠቅ፣ የጥበቃና የምናኔ ተምሳሌት ሆኖ ተገልጧል፡፡ ግብጻውያን ደግሞ የተቀበሩ ሰዎችን አጋንንት እንዳይደርሱባቸው በመቃብራቸው በር በድንጋይ ላይ የንሥርን ምስል ያስቀርጹ ነበር፡፡ ይጠብቃቸዋል ብለው፡፡ በግሪክ አፈ ታሪክ የአማልክት ንጉሥ የሚባለው ዜውስ በንሥር የሚመሰል ነበር፡፡ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች እጅግ ለሚያከብሩት የሌላ ወገን ሰው የንሥርን ላባ በመስጠት ክብራቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጡ ነበር፡፡ ሞቼ የተባሉት የፔሩ ሕዝቦችም ንሥርን ያመልኩት ነበር ይባላል፡፡


ንሥር ይህንን ያህል ቦታ በሕዝቦች ባሕል ውስጥ ሊይዝ የቻለው በተፈጥሮው በታደላቸው የተለያዩ ጸጋዎች የተነሣ ነው፡፡
ንሥር ከእንስሳት ሁሉ ወደ ሰማይ በመነጠቅ የሚተካከለው የለም፡፡ እርሱ የሚደርስበትን የሕዋ ከፍታ የትኛውም ዓይነት ወፍ አይደርስበትም፡፡ አንዳንድ አዕዋፍ እስከ ተወሰነ ድረስ ቢከተሉትም እንኳ እርሱ ግን ጥሏቸው ማንም በማይደርስበት የሰማይ ጥግ ብቻውን ይንሸራሸራል፡፡ ለዚህም ነው ጥንታውያን ሰዎች በሐሳብ የመምጠቅ፣ ማንም ከማይደርስበት የጸጥታ ሕዋ ላይ አእምሮን የማሳረግ፣ ተራ ነገር ማሰብና ተራ ነገር መሥራት ከሚችሉ ደካማ ልቦች ርቆ በሉዓላዊ ሐሳብ ላይ የመምጠቅ ምሳሌ ያደረጉት፡፡


ታድያ ይኼ ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ከቁራዎችና፣ ከሌሊት ወፎች፣ ከጥንብ አናሣዎችና ከድንቢጦች፣ ከተባዮችና ከነፍሳት ጋር እዚህ ምን ታደርጋለህ? በወረደ ሐሳብ ለምን ትመስላቸዋለህ? ውጣ ወደላይ፤ ሂድ ዐርግ፣ ምጠቅ ተመሰጥ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስ ዝንብና ትንኝ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስም ነፍሳት፣ እስከ ተወሰነም ቦታ ድንቢጦችና የሌሊት ወፎች፣ እስከ ተወሰነውም ቁራዎችና ጥንብ አንሣዎች ይከተሉህ ይሆናል፡፡ ሐሳብህን ከፍ፣ አእምሮህንም ሉዓላዊ፣ ልቡናህንም ምጡቅ፣ አመለካከትህንም ከፍ ያለ ባደረግከው ቁጥር ግን ደካቹ ከሥር እየቀሩ ከሚመስሉህ ከንሥሮች ጋር ብቻ በጸጥታው ሕዋ ላይ ትንሳፈፋለህ፡፤ ሂድ ዐርግ፡፡


ንሥር እጅግ አስደናቂ የሆነ የማየት ችሎታ የተሰጠው ፍጡር ነው፡፡ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ውስጥ አንዲትን ትንሽ ጥንቸልን አንጥሮ ማየት ይችላል፡፡ የንሥር ዓይን ከጭንቅላቱ በተነጻጻሪ ሲታይ እጅግ ታላቅ ነው፡፡በንሥር ዓይን ውስጥ በአንድ ሚሊ ሜትር ስኩዌር ረቲና አንድ ሚሊዮን ለብርሃን ስሱ የሆኑ ሴሎች አሉት፡፡ ሰዎች ስንት ያለን ይመስላችኋል? ሁለት መቶ ሺ ብቻ፡፡ የንሥር አንድ አምስተኛ ማለት ነው፡፡ ሰው ሦስቱን መሠረታዊ ቀለሞች ብቻ ማየት ሲችል ንሥር ግን አምስቱን ማየት ይቻለዋል፡፡ እንዲያውም ከሩቁ አንጥሮ በማየት ንሥርን የሚተካከለው እንስሳ የለም የሚሉ ጥናቶችም አሉ፡፡


ንሥር የሚፈልገውን ለማሰስ እስከ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ ይዞራል፡፡ ሲያገኝ ግን ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ በሚያድነው ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት› የሚለውን የአማርኛ ብሂልና ‹jack of every thing master of non› የሚለውን የእንግሊዝኛ አባባል በደመ ነፍስ ዐውቆታል፡፡ ከትኩረቱ ፈጽሞ ንቅንቅ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ግርዶሽ፣ ምንም ዓይነት መሰናክል፣ ምን ዓይነት መደለያ አያዘናጋውም፣ ተስፋም አያስቆርጠውም፡፡ የዚያን የአደኑን ነገር በንቃትና በትጋት እስከ መጨረሻ ይከታተለዋል፡፡ እንዲሁ አይወረወርም፤ ጊዜና ሁኔታ ይመርጣል፡፡ ጊዜና ሁኔታ ሲገጥሙለት ትኩረቱን ሰብስቦ በመወርወር ታዳኙን ይሞጨልፈዋል፡፡


ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ደጋግመህ አስብ፤ ለመወሰን ጊዜ ውሰድ፤ ዙር ተዟዟር፡፡ ልፋ ድከም፤ አንድ ጊዜ ለመቁረጥ ሺ ጊዜ ለካ፡፡ በመጨረሻም ዒላማህን ለይ፡፡ አስተካክል፡፡ ትኩረትህንም በዒላማህ ላይ ብቻ አድርግ፤ ምንም ዓይነት ማታለያ፣ ምንም ዓይነት መደለያ፣ ምንም ዓይነት ማሰናከያ፣ ምንም ዓይነት ፈተና፣ ምንም ዓይነት ተስፋ መቁረጥ ከዓላማህ ሊያግድህ አይገባም፡፡ ማየትና ማሰብ ያለብህ ሁሉም ሊያየውና ሊያስበው የሚችለውን ተራ ነገር አይደለም፡፡ ሊታይ የማይችለውን ለማየት፣ ሊለይ የማይችለውን ለመለየት፣ ሊተኮርበት ያልቻለውን ለማተኮር ጣር፡፡ ዒላማህን ካገኘህ አትልቀቅ፤ ጊዜና ሁኔታ አመቻችና ዒላማህ ላይ ተወርወር፡፡ ያንተ ከመሆን ማንም አያግደውም፡፡


ንሥር በምንም ዓይነት የሞቱ እንስሳትን አይበላም፡፡ እርሱ እቴ፡፡ በሕይወት ያለውን እንስሳ የገባበት አሳድዶ፣ ከተደበቀበት ጠብቆ አድኖ ይበላዋል እንጂ እርሱ እንደ ቁራና ጥንብ አንሣ የሞተ ላይ አያንዣብብም፡፡ እንደ አራዳ ልጆች ከተበላ ዕቁብ ጋር አይጨቃጨቅም፡፡ ቀላል ነገር ቢያጣ በግና ፍየልም ቢሆን ተወርውሮ አድኖ፣ ከዐለት ላይ ፈጥፍጦ እንደ አጥንት ወዳጅ አበሻ ቅልጥም ሰብሮ ይበላል እንጂ የሞተ ጥንብ ሲያልፍም አይነካው፡፡ ያቺን ከባዷንና በድንጋይ የተሸፈነችውን ዔሊ እንኳን ከዐለት ስባሪ ላይ ከስክሶ ድንጋይዋን አራግፎ ይበላታል እንጂ  እንደ አበሻ ማን እንዳረደው ያላወቀውን ነገር አይበላም፡፡


ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ልቡናህንና ኅሊናህን፣ አእምሮህንና መንፈስህን ምን እንደምትመግባቸው አስብ፡፡ የሞተ፣ የማይሠራ፣ የተበላሸ፣ ጊዜው ያለፈበት፣ ቁራና ጥንብ አንሣ የሚጫወቱበትን አትመግበው፡፡ ፊልምና ፕሮፓጋንዳ፣ ዋዛና ፈዛዛ፣ የወረዱና የበከቱ አስተሳሰቦችን አትመግበው፡፡ ከተፋና ለብለብ ሐሳቦችን አትጋተው፡፡ ይልቅ አድን፣ ድከም፣ ልፋ፣ ተሟገት፣ ተመራመር፣ እንደ ዔሊ ድንጋይ የከበደውን አስተሳሰብ ገልብጠህ፣ ፈንክተህ ተመገብ፤ ድካምና፣ ጽሞና፤ ማሰብና መመርመር የሚሻውን ንባብ ውደድ፤ ሳይለፉና ሳይደክሙ እንደ ሞተ እንስሳ ሥጋ የትም የሚገኘውን ነገር ሳይሆን ጥረትና ግረት የሚሻውን፤ ላብ ጠብ የሚያደርገውን ሞያና እንጀራ ፈልግ፡፡


ንሥር ዐውሎ ይወዳል፡፡ ሰማዩ ሲጠቁርና ደመናው ሲሰበሰብ ወጀቡም ሲያይል ሌሎች አዕዋፍ በዐለት ንቃቃትና በጫካው ችፍርግ ውስጥ ይደበቃሉ፤ በቤት ታዛ ሥርም ይሠወራሉ፡፡ ንሥር ግን ደስ ይለዋል፡፡ ወጀቡና ዐውሎው ሲጀምር ንሥር የንፋሱን ኃይል በመሞገት የራሱን ጥንካሬ ይለካበታል፡፡ የነፋሱን አቅጣጫ በመከተልም ይበራል፡፡ ራሱን ወደ ላይ ለማምጠቅና የከፍታውን ጫፍ ለመጨበጥ ይጠቀምበታል፡፡ በዚያ ጠንካራ ነፋስ ትከሻ ላይ ሲጫን ነው ንሥር ዕረፍት የሚወስደው፡፡ ክንፉን ብቻ ዘርግቶ በዕረፍት ስሜት ከደመና በላይ የኃያሉን ዐውሎ ዐቅም ተጠቅሞ ይንሸራሸራል፡፡


አንተንም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- መከራንና ፈተናን አትፍራ፤ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥም ቢሆን መንገድ አለና፡፡ መከራውንና ችግሩን፤ ፈተናውንና ግብግቡን የአዳዲስ ሐሳቦች መነሻ፤ የጥንካሬህ መለኪያ፤ ዐቅምህን የምትሰበስብበት አጋጣሚ፣ ወደላይ የምትመጥቅበትና ከችግር ደመናዎች በላይ የምትንሳፈፍበት ዕድል አድርገው፡፡ እንደ ሌሎች ወፎች ከመከራው አትሽሽ፤ ከችግሩም አትደበቅ፤ መከራን ለበረከት ተጠቀምበት፡፡

ለእግዜር የተላከ ደብዳቤ

ለእግዜር የተላከ ደብዳቤ
(ገጣሚ ጌታቸው ይመር )
----------------------
እንደምነህ እግዜር
ሰማይ ቤት እንዴት ነው
እመጣለሁ ብለህ ቆየህሳ ምነው?

እኛማ.....
ለእልፍ አላፍ አለቃ
ማመልከቻ ፅፈን
ለወፈ ሰማይ ህዝብ
መድረክ ላይ ለፍፈን
ፆለት ቤታችንን
እኛው ላይ ቆልፈን
የምድር አተካራ
ህግጋቱን አልፈን ደብዳቤ ላክንልህ፤

አይንህን ካየነው
ሁለት ሽ ዘመን
እንደቀልድ አለፈ
የመምጣትህ ተስፋ እየኮሰመነ
መቅረትህ ገዘፈ...

እንደውም እንደውም...
‹‹በእመጣለሁ ተስፋ
ሁለት ሽ ዘመን
ቀጥሮን ከጠፋ
በቀጠሮው ሰአት
መምጣት ከተሳነው
እግዜር አበሻ ነው›› እያሉ ያሙሃል

እኔ ምን አውቃለሁ...
አመስግነው ሲሉ እልልታ የማቀልጥ
ቃሉን ስማ ሲሉኝ ...ሰባኪው እግር ስር በደስታ እምቀመጥ
እግዚኦ በሉ ሲባል ...እንባየን የማፈስ
ሃሌ ሉያ ሲሉኝ ...በሳቅ ልቤ እሚፈርስ
ምናምኒት እውቀት ውስጤ ያልፀደቀ
እንበረከክበት ጉልበቴ ያለቀ
እኔ ምን አውቃለሁ...

ግን አንተ ደህና ነህ?
ከምር እንደሚያሙት ምፅአት ቀረ እንዴ ?
የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አትከፋም አንዳንዴ!

ከሆነስ ሆነና ሰማይ ቤት እንዴት ነው
አብረሃም ሰላም ነው...
እዛስ ቤት ገነባ ዛሬም በድንኳን ነው ?

እኛማ ይሄውልህ...
በቤት ኪራይ ችንካር እየተሰቀልን
‹‹ኤሎሄ›› እንላለን ጎጆ እንድጥልልን....
ወደላይ ገነባን ወደጎን አሰፋን
ወደላይም ከላይ ወደጎንም ከጎን
እንደጉድ ተገፋን
ቤት ለእንግዳ ማለት ጭራሹኑ ጠፋን !!

አባታችን ሙሴ እነዴት ነው ለክብሩ
ውቂያኖስ መክፈያው ደህናናት ብትሩ?

እኛማ ይሄውልህ....
እንጀራ ፍለጋ ባህር ስናቋርጥ
የተስፋዋን ምድር አሸዋ ሳንረግጥ
የትም ውሃ በላን የትም አሳ ላሰን
ን ገ ር ል ን ና ብትሩን ያውሰን....

እናልህ እግዜር ሆይ....
ከተስፋዋ ምድር ወደሌላ ተስፋ አለን እየኳተን
መሄጃው ሲገርመን መመለሻ መንገድ መቆሚያ ቦታ አጥተን...!

ላባታችን ሙሴ እንደምትልልን...
‹‹የመሄድ ዘመን ነው
ባህር የመሻገር
‹‹ዱላህን ላክልን›› ብሎሃል በልልኝ...

ሰማይ ቤት እንዴት ነው? ....ዳዊትስ ደህና ነው?
ዛሬም ይዘምራል ...ዛሬም ይፎክራል ?
ሰላም ነው ጠጠሩ .... ሰላም ናት ወንጭፉ?
እዛስ አቅል ገዛ ጎሊያድ ተራራው ጎሊያድ ግዙፉ?

እልፍ አላፍ ጎሊያድ ከቦን ሲደነፋ
ወንጭፉን ጠቅልሎ ምነው ዳዊት ጠፋ ?
ብሎሃል በልልኝ!!

ለረከሰ ጠጠር ለሞላ ወርዋሪ
‹‹ወንጭፍህን ስጠው ለዚህ ታሪክ አውሪ››
ብለህ እዘዝልን!!

እንዴት ነህ ጌታ ሆይ... ሰማይ ቤት እንዴት ነው?

የሙሴ አልጋ ወራሽ እያሱ ሰላም ነው....
ያቆማትን ፀሃይ ግቢ ቢላት ምነው...
ያው እንደምታውቀው
አስራ ሶስት ወራት ነው ፀሃይ የምንሞቀው...
ኧረ ፀሃይ በዛ
ኧረ ፀሃይ በዛ
ኧረ ፀሃይ በዛ
የመጣው ወር ሀሉ ፀሃይ እያዘለ
የተሸመው ሁሉ ‹ፀሃይ ነኝ› እያለ
የአስራ ሶስት ወር የግዜር ፀሃይ
የአስራ ሶስት ወር የሰው ጀምበር
ባቃጠላት ምድጃ አገር
ምን ታምር ሊኖር ይችላል ፀሃይ ሁኖ እንደመፈጠር....

ኧረ እግዜር በናትህ....
ኧረ እግዜር በናትህ...በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!

እናልህ እግዜር ሆይ ማጣፊያው አጥሮናል
ስም ያለው ሞኝ ነው ሁሉም ይጠራናል...
ጳውሎስ ሲሉን ...አቤት
ጴጥሮስ ሲሉን ...ወይየ
ይሁዳ ሲሉንም አቤት እንላለን
ስማችንን ሸጠን ...ሰላሳ ጭብጨባ እንቀበላለን

ተወው የኛን ነገር ...ሰማይ ቤት እንዴት ነው ....
ሂዋንስ ደህና ናት?
ያው የልጅ ልጆቿ
በእግሯ ተተክተው
የፍሬው ሲገርምህ
ግንዱንም አንክተው
ለፍጥረተ አዳም
ባይኑ ያገምጡታል
ሰይጣንም ደህና ነው
ኑሮ ተስማምቶታል....
ሰውን ለማሳሳት
ላይ ታች ማለት ትቷል
ሳይጠራው የሚጎርፍ ህዝብ በዝቶለታል...!

ኧረ እግዜር በናትህ በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!!

Sunday, August 3, 2014

እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ

ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር
እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ
ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤
በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ ፤
ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ
እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን
የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ፡፡
ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት
በማይቻል ዕንቊ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡
መልክአ ማርያም
ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ
እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና ዕርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ ዐበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡
እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽዕ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡
እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ መድኃኔዓለምን በማህጸንዋ ጸንሳ ዘተኝ ወር ፤ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡
ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር /መዝ 136¸8/ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሎአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡ የዜማም ጊዜ ደረሰ የቀረ… ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ” ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ /መኃ 2¸1ዐ-13/
ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን መከራ ስድት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18¸4/
የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ /መዝ 14¸13/ የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን ዐረፈች፡፡
እመቤታችን ጥር 21 ቀን ዕረፍት በሆነበት ዕለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ ዕረፍት /የመቃብር ቦታ/ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል፡፡ እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች ፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ /መዝ 44¸9/
ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ” ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/ ሰጥታው ዐረገች፡፡
እመቤታችን ለቶማስ ሰበን /መግነዟን/ ሰጥታው ዐረገች
ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን;” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን /መግነዟን/ ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡
ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ /ረዳት/ ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ /ዋና/ ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡
ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና ዕርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጻመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡
የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ /በጾመ ፍልሰታ/ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡
ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች ዕመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን ፤ ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ጾመ መድኃኒት ያድርግልን- አሜን ፡፡

Thursday, July 31, 2014

ከዲ/ን መስፍን ደበበ
እርሱ እናቴ እኔን ቅሪት እያማጠኝ፤
በልጅነት ሊገላገል በሐሳብ ያረገዘኝ፤
በማኅፀን ሰፋድሉ በትምህርቱ እኔን ስሎ፤
በመዶሻው እኔን ጠርቦ አስተካክሎ፤
እጄን ይዘህ አለማምደህ እንዲያ ስድህ፤
ቃለ ነገር ቃለ ምሥጢር እየጋትህ፤
ጠንካራውን ጥሬ ቃሉን አስቆርጥመህ፤
አንተ አብይ ባሕር የትምህርት ውቅያኖስ፤
ምርጥ ዕቃ ማዕዘን ዕብነ አድማስ፤
በእንቁላል ቅርፊት ቀድቼ የረካሁኝ ከአንደበትህ፤
ርዕሰ እውቀት አንተ አፈ ዝናም በትምህርትህ፡፡
አሕዛበ-ምድር ማንነቴን በጠብታህ ጎበኘሃት፤
የነፍሴን እርሻ አጥግበህ በልምላሜ ከደንካት፡፡
ሕሊናዬን በተመስጦ መንኮርኩር ስታከንፋት፤
ከታችኛው ከእንጡረጦስ ከበርባኖስ ስታጠልቃት፤
ዖፈ ጣጡስ መጥቀህ በረህ የነገርኸኝ፤
እንደ ሙሴ ከእግረ ታቦር ያላቆምኸኝ፤
አለማወቅ ጥቁር ካባ፤ የጨለማን መጋረጃን ያራቅህልኝ፤
ኢትትሃየድ እያለ ወራሴን ስታለምደኝ፤
ምሥጢሩን ስትቀዳ ዘቦቱን ስትነግረኝ፤
የሰብዕና ዘበኛዬ እኔን በትምህርቱ ንቅሳት ሲነትበኝ፤
ያኔ ነበር የነቀሰኝ በልቡናዬ ሕያው ቃሉን የከተበኝ፤
በጉልጓሎ በእርሻው ቦታ የጠመደኝ፤
እያረሰ ጅራፍ ቃሉን ጆሮዬ ላይ ሲያጮህብኝ፤
ከሃያው ክንድ ከመቅደሱ ከሚፈልቀው፤
ከዙፋኑ ከቃል ሥግው ከሚፈሰው፤
እንደ መስኖ ሊቀላቀል ከሚወርደው፤
ከእኔ ሕይወት ከሸለቆ ከአዘቅቱ ሲንዶሎዶል፤
የመብል ዛፍ ፍሬ በኩር ሲያበቅል፤
ያኔ ነበር ስሜ ሽቶ ከጌታ ስም ሲቀላቀል፤
ሃይማኖት የፍቅር እሳት ሲንቀለቀል፤
ተቆጠርኩኝ ግብር ገባሁ ከቤተ ወንጌል፡፡

Sunday, July 27, 2014

ጾም



==> ~ † ~ “ጾም ትፌውሥ ቁስለ ነፍስ ወታፀምም ዂሎ ዘሥጋ ፍትወታት
ትሜሕሮሙ ጽሙና ለወራዙት።”~ † ~ <==

==> “መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም’’ ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፰ (8፥8) ለዚህ ነው ደንኤልም በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። ያለው ት/ዳን. ፲፥፪-፫ (10፥2-3) ያለም መድሃኒት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንኑ ሲያስረግጥ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል በማለት በማቴ. ፬፥፬ (4፡4)

==> በት/ኢዩ. ፪፥፲፪-፲፫ (2፡12-13) አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።

==> ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ። ት/ኢዩ.፩፥፲፬ (1፥14)

==> ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ማለት ነው፡፡ ወይም ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጉመዠውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ዳዊት በመዝ.108፥25 ላይ ሰውነቴ በፆም ደከሙ ጉለበቴም ቅቤን በማጣት ከሳ ያለው፡፡ ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና አለው፡፡

==> ከጥንት ከበሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የበሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውኃ ባፋቸው አይገባም ነበር። ዘጸ.34፥28።
በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰውና ቁጣው የሚበርደው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር። ዮና 3፥5-10
==> በአዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መደኃኒታችን ኢየሰሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው። ማቴ.4፣2፤ ሉቃ.4፣2 ፡፡ በዚህም በስስት፣በፍቅረ ነዋይና በትዕቢት የሚመጣብንን ጠላት ዲያብሎስን በጾም ድል እንደምናደርገው አሳይቶናል። ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር ርኩስ መንፈስ በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ማቴ.17፥21፤ማር. 9፥2። በመሆኑም ጾም ለእኛ ታላቅ ጸጋና ኃይላችን ነው፡፡
==> ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እያሉ ነበር። የሐዋ.13፥2፡፡ ይህም የሚያመለክተው ጾምና ጸሎት የማይነጣጠሉ መሆናቸውና ጾምን ከጸሎት ጋር ስናስተባብር መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀርበን ነው፡፡ በጾም የተዋረደ እና ለጸሎት የተጋ ሰውነት ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ የተዘጋጀ በመሆኑ እግዚአብሔር ያዝዘናል እኛም እንታዘዛለን።

==> የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ ከኃጢአት ቁራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ለአምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን ሥጋንና ቅቤን ወተትና ዕንቁላልን ማራቅ ታዟል፡፡ባልና ሚስትም በአንድ ምንጣፍ አይተኙም፡1ቆሮ.6፣5፡፡ ‘ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ነዑድ ነው፣ክቡር ነው፡፡’’ እንደተባለ ጾመኛው ለምሳው ወይም ለእራቱ ያለወን ወጪ ነዳያንን እንዲረዳበት ለደኩማን ድርጅት ቢሰጥ ወይም በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን ቢመጸውት ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡
==> ጾም የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ ከኃጢያት ለመንጻት ስለራስ የታሰበውን ለነዳያን በመስጠት የሚጾም መሆኑን መረዳት አለብን ፡፡ ጾም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ነው፡፡ በዲዲስቅልያ 1፡5 ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው ተብሏል፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዙትን በስደትና በምርኮ ያሉትንም በጾም ወራት ማስታወስና ስለ እነርሱ መጸለይ ይገባል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ክፉ ከማየት ክፉ ከመናገር እና ክፉ ከመስማትም ጥምር መጾም እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

ስለዚህ በዚህች በተቀደስች ወርሐ ነሐሴ ጾመ ፍስለታ ከመጾማችንና ቤተክርስቲያን ሄደን ከማስቀደሳችን ጋር አብሮ ጎን ለጎን መደረገት ያለበትንም በማለመርስታ የተቸገሩትን በመርዳት መልካምና አርአያ የሆነ ተግባር በማድረግ እንዲሆን በማለት መልካም የበረከት ጾም እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፡፡

ጾም- ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው!!

ጾም- ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው!!

ጾም- ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው!!

ጾም መድኃኒት ናት፡፡ አወሳሰድዋን በትክክል ላላወቁ ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒትየሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱ እንደምትወሰድ፣ በምን ያህል መጠን (Dosage) እንደምትዋጥ፣ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው ወራትና በየትኛው የአየር ሁናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚሄዱና የማይሄዱ ምግቦችን እንዲሁም ሌሎች ከእርሷ ጋርየማይስማሙ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡

እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብተን የማንወስዳት ከሆነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡ ስለዚህ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ዘሥጋመድኃኒት በትክክል ከወሰድነው ከሕመማችን እንፈወሳለን፤ የነፍሳችንን ደዌ ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ በበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡
ጾም ሁለመናችንን የምንለውጥበት መሣርያ ነው፡፡ ምክንያቱም የጾም መሥዋዕት ማለት ከምግብ ብቻ መከልከል ሳይሆን ከኃጢአት ሁሉ መከልከል ነውና፡፡ ስለዚህ እየጾምኩ ነው እያለ ራሱን ከምግብ ብቻ የሚከለክል ሰው ካለ እርሱ ጾምን እያቃለለና እያጥላላ ነው ማለት ነው፡፡

እየጾማችሁ ነውን?

እንግዲያስ መጾማችሁን በተግባር አሳዩኝ፡፡

“እንዴት አድርገን እናሳይህ?” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡

እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፡- ደሀው እርዳታችሁን ፈልጎ እንደሆነ ቸርነትን አድርጉለት፤ የጠላችሁትን ሰው ካያችሁት ከእርሱ ጋር ፈጥናችሁ ታረቁ፤ ባልጀራችሁ ተሳክቶለት ስታዩት በእርሱ ላይ ቅናት አትያዙ፤ ቆነጃጅትን በመንገድ ሲያልፉ ስታዩ በዝሙት ዓይን አትመኙ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያደረጋችሁ በትክክል መጾማችሁን አሳዩኝ፡፡

በሌላ አገላለጽ አፋችሁ ብቻ ሳይሆን ዐይናችሁ፣ እግራችሁ፣ እጃችሁ፣ በአጠቃላይ የሰውነታችሁ ሕዋሳቶች በሙሉ መጾም አለባቸው፡፡

እጆቻችሁ ከመስረቅና የእናንተ ያልሆነውን ከመውሰድ ይጹሙ፤
እግሮቻችሁ የኃጢአት ሥራን ለመፈፀም ከመፋጠን ይጹሙ፤
ዐይኖቻችሁ ውጫዊ በሆነ ውበት ምክንያት ከመቅበዝበዝ ይጹሙ፡፡
ጥሉላትን (የፍስክ ምግብ) እየበላችሁ አይደለም አይደል? እንግዲያስ በዐይኖቻችሁም ክፉ ነገርን አትብሉ፡፡ የሚታዩ ነገሮች ለዐይን ምግቦች ናቸውና፡፡ ጀሮዎቻችሁም ይጹሙ፡፡ የጀሮ ጾም ሐሰተኛ ወሬንና ሐሜትን አለመስማትና ይህን የመሳሰለ ነው፡፡

አንደበታችሁም ከከንቱ ንግግር ይጹም፡፡
ዓሣንና ሌሎች ጥሉላትን ከመብላት ተከልክለን ሳለ ነገር ግን ወንድሞቻችንን በሐሜት የምናኝካቸውና የምንበላቸው ከሆነ ምን ጥቅም አለው?

ወንድሙን የሚያማና የሚነቅፍ ሰው እርሱ የወንድሙን አካል ያቆስላል፤ ሥጋውንም ይበላል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ይህን አስመልክቶ እጅግ የሚያስደነግጥ ንግግርን እንዲህ ሲል የተናገረው፡- “እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” /ገላ.5፡15/፡፡

ስታሙ በጥርሳችሁ የወንድማችሁን ሥጋ አትነክሱም፡፡ በክፉ ንግግራችሁ ግን የወንድማችሁን ነፍስ ትነክሳላችሁ፤ ታቆስሉትማላችሁ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ራሳችሁን፣ ወንድማችሁንና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ትጎዳላችሁ፡፡
አንደበታችሁ ክፉ ነገርን ከመናገር ካልጦመ ጉዳቱ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሐሜታችሁ እናንተን የሚሰማ ወንድማችሁም የሐሜታችሁ ተባባሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት እርሱንም በደለኛ ታደርጉታላችሁ ማለት ነው፡፡ እርሱም የራሱን ኃጢአት እንዳይመለከት ስላደረጋችሁት ሳያውቅ ከሐሜተኞች ጎራ ይቀላቀላል፡፡ በዚህ ሰዓት የሌሎች ወንድሞቹን ድካም እየተመለከተ እርሱ ግን በመጦሙ ትልቅ የጽድቅ ሥራን እንደፈጸመ ቆጥሮ ይኩራራል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ሊታይ የሚገባው ሌላ ትልቅ ቁም ነገርም አለ፡፡ ይኸውም እናንተ ወንድማችሁን ስታሙ የሚያደምጧችሁ ሰዎች የምታሙትን ወንድማችሁን በመንቀፍ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ይልቅ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንንም ጭምር ይነቅፋሉ እንጂ፡፡ በተለይ ሰማዕያኑ ኢ-አማንያን ከሆኑ ያንን የምታሙት ሰውዬ ብቻ “አመንዝራ” ብለው አያበቁም፡፡ ከዚያ አልፈው ቤተ ክርስቲያንም የአመንዝራዎች ቤት እንደሆነች ያስብዋታል እንጂ (ሎቱ ስብሐት!)፡፡ ስለዚህ እንዲህ ስታደርጉ የእግዚአብሔርን ስም ታሰድባላችሁ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መልካም ስናደርግ እግዚአብሔር በእኛ ምክንያት እንደሚመሰገን ሁሉ ክፉ ስናደርግም በዚያው ልክ ስሙ ይዋረዳል፤ ይሰደባልምና፡፡
ሌላው ይህ እናንተ የምታሙት ወንድማችሁ በልቡ እናንተን መጥላት እንዲጀምርና የባሰ ኃጢአት እንዲሠራም ትገፋፉታላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት በማይመለከታችሁ ነገር እጃችሁን በመክተታችሁ በራሳችሁ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን ታመጣላችሁ፡፡ ያውም በወርሐ ጦም፡፡
ከእናንተ መካከል፡- “ዋሽቼ ስለ ወንድሜ ክፉ ነገርን ካልተናገርኩ ነገር ግን እውነት የሆነውን ነገር ብናገር (የሠራው ኃጢአትም ቢሆን) ምን ነውር አለው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ግድ የላችሁም! የምታወሩት ነገር እውነት ቢሆንም እንኳ አሁንም ንግግራችሁ ከነቀፋ አያመልጥም፡፡ “እንዴት ሆኖ?” ብላችሁ ልትጠይቁኝ ስለምትችሉ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ ልስጣችሁና ንግግራችሁ እንዴት ብሎ ክፉ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ስምንት ላይ የምናገኘው አንድ ፈሪሳዊ አለ፡፡ ይህ ፈሪሳዊ ስለ ቀራጩ ወንድሙ የተናገረው ነገር እውነት ነው አይደል? ታድያ እውነቱን ስለተናገረ ተጠቀመ ወይስ ተጎዳ? ንገሩኝ እንጂ? ፍጹም አልተጠቀመም! እንዲህ በማለቱ (እንደ እናንተ አባባል “እውነትን በመናገሩ”) ባዶ እጁን አልተመለሰምን? በመጸለዩና በመጦሙስ ምን ረብሕ አገኘ? እስኪ አሁንም ልጠይቃችሁና እናንተም መልሱልኝ፡፡ ቀራጩ ኃጢአተኛ አልነበረምን? ከወንጌሉ እንደምናነበው ያ ቀራጭ ኃጢአተኛ እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ፈሪሳዊው በጸሎቱና በጦሙ መካከል የራሱን ኃጢአት ከማሰብና ከማሳሰብ ይልቅ ወንድሙን እያማ ስለነበረ ወደ ቤቱ የተመለሰው የጦምን ዋጋ ሳያገኝ ባዶውን ነው፡፡
ወንድሞቼ! “እከሌ እኮ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ሠርቷል” ብላችሁ የምታሙትን ወንድማችሁ ከዚያ ኃጢአቱ ነጻ እንዲወጣ ትፈልጋላችሁን? እንግዲያስ ስለ ኃጢአቱ አልቁስለት፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩለት፤ ለብቻ ወስዳችሁም ምከሩት እንጂ አትሙት፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ ጽፎላቸው ነበር፡- “ነገር ግን ወዳጆች! እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። ስመጣእንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል፤ እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፡፡ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፡፡ እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬእፈራለሁ” /2ቆሮ.12፡19-21/። ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በትልቁ ደግሞ እንደ ጌታችን “ኃጢአተኛ ነው” የምትሉትን ወንድማችሁ ውደዱት፡፡ ለብቻው አድርጋችሁ ስትነግሩትም አመጣጣችሁ እርሱን ለመምከርና ለመገሰጽ ደግሞም ከኃጢአቱ እንዲመለስ እንጂ እርሱን ከመጥላታችሁ የተነሣ እንዳልሆነ አስረዱት፡፡ ስለዚህ በትክክል ካለበት ደዌ እርሱን መፈወስ ስትፈልጉ ወደ እርሱ መሄድን አትፍሩ፤ ጥፋቱን ለመንገርም አትፈሩ፡፡ ሐኪሞችን አይታችሁ ከሆነ አንድ አስቸጋሪ ታማሚን ለማከም መጀመርያ ቀስ ብለውና ጊዜ ወስደው ታማሚዉን ያሳምኑታል፤ ከዚያም መራሩን መድኃኒት ይሰጡታል፡፡ ታካሚውም በሽታው የሚድን ከሆነ ይፈወሳል፡፡ ሐኪሙን የሚያመሰግነው ግን ሲድን ነው፡፡ እናንተም እንደዚህ ሐኪም መሆን አለባችሁ፡፡ ከምታሙት ይልቅ የወንድማችሁን ቁስል የበለጠ እንዳይመረቅዝ ፈጥናችሁ ወደ ሐኪም ቤት (ወደ ቤተ ክርስቲያን) ውሰዱት፡፡ ከዚያም ሐኪም (ካህን) እንዲያየው አድርጉ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ እናንተም ወንድማችሁም በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡ እውነተኛ ጦም ጦማችሁ ማለትም እንዲህና ይህን የመሰለ መልካም ምግባር ስታደርጉ ነው፡፡
ሐሜተኞችን ብቻ ሳይሆን ክፉ ንግግርን (ዘፈንም ያጠቃልላል) የሚያደምጡትንም ጭምር ጀሮዋቸውን ከዚሁ ቆሻሻ እንዲያርቁ እጽፋለሁ፡፡ ከመዝሙረኛው ጋር በመሆን እንዲህ በሉ፡- “ወንድሙን በስውር የሚያማን እርሱን አሳደድሁ” /መዝ.101፡5/፡፡ ከእናንተ ጋር ወንድሙን ለማማት ብሎ የመጣ ካለ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፡- “ስለ እርሱ መልካም ነገር የምትናገርለት አሊያም ደግሞ የምታመሰግነው ወንድም ካለህ መልካም መዐዛ ያለው ጨዋታህን ለማድመጥ ጀሮዬ ክፍት ነው፡፡ ክፉ ንግግርን የምታወራ ከሆነ ግን ይህን ቆሻሻ ወደ ጀሮዬ አስገባ ዘንድ ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ወንድምህ ክፉ መሆኑን ብትነግረኝ ምን ይረባኛል? ይልቁንም እንዲህ ስታደርግ ራሴን እንድጎዳና ያለኝን እንዳጣ ታደርገኛለህ፡፡ ወንድሜ! ስለ ወንድማችን ጥፋት ከምናወራ ይልቅ ስለ ራሳችን ኃጢአት ብናወራ የተሻለ ነው፡፡ የሠራናቸውን ጥፋቶች ይቅርታ እንዴት እንደምናገኝባቸው ብንጨነቅ መልካም ነው፡፡ ስለ ራሳችን ኃጢአት ብቻ ብንነጋገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ወንድሜ! ንገረኝ እስኪ! በዓይናችን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ሳናጸዳ የወንድማችንን ጕድፍ በማውራታችን የሚደረግልን ምሕረት ይኖራልን? በልቡናችን ጀሮ ላይስ ለምን ሌላ ኵክ እንጨምራለን? …”
እንግዲያስ ይኸንን አውቀን በሁለንተናችን እንጡም፡፡ ክፉ ከመናገር እንጡም፤ ክፉ ከመስማት እንጡም፤ ክፉ ከማየት እንጡም፤ ወደ ክፉ ከመሄድ እንጡም፤ ክፉ ከማድረግ እንጡም ... የአዋጅ ጦም ሲገባ መንፈሳዊ የበጋ ወራት እንደገባ ልብ እንበል፡፡ የጦር መሳሪያችንን እንወልውል፤ ከእርሻቸው አዝመራውን የሚሰበሰቡት ገበሬዎች ማጭዳቸውን ይሳሉ፤ ነጋዴዎችም በከንቱ ገንዘባቸውን ከማባከን ይከልከሉ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባትም መንገዳቸውን ያቅኑ፤ ወደ እግዚአብሔርመንግሥት የምትወስደው ጎዳና ቀጭንና ጠባብ ናትና በጥንቃቄ እያስተዋልን እንጓዝ …
ወንድሞቼ! በበሽታ ምክንያት ከምግብ ባለ-መከልከላችን የሚወቅሰን ጤናማ ሰው የለም፡፡ ከዚሁ በላይ ደግሞ የዋህና ሰውን አፍቃሪ ደግሞም ከምንችለው በላይ ምንም የማይጭንብን አምላክ አለንና፡፡ የእርሱ ፍላጎት እኛ ከምግብ እንድንከለከል፤ ወይም እንዲሁ “ሰው ምን ይለኛል” ብለን እንድንጦም፤ ወይም ሆዳችን ባዶ ሆኖ የረሀብ ስሜት እንዲሰማን ማድረግ ሳይሆን ከማንኛውም ክፉና ዓለማዊ ምግባር ጦመን ለትሩፋተ ሥጋ ለትሩፋተ ነፍስ እንድንተጋ ነውና፡፡ ራሳችንን በተስተካከለ ሕይወት የምንመራ፣ መብላት ያለብንን ያህል መጥነን የምንበላ፣ ፍላጎታችንን ሁሉ ወደ ሰማያዊ ነገሮች የምንመልስና መላ ዘመናችንም መልካም ነገርን ብቻ የምናደርግ ብንሆን ኖሮ እሴተ ጦምን (የጦምን ዋጋ) ለማግኘት ብለን መጦም ባላስፈለገን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሰው ልጆች ስንባል በተፈጥሮአችን ግዴለሾችና ምቾትን የምንሻ ስለሆነን ከምድራዊ አባትም ሆነ ከምድራዊት እናት በላይ ስለ እኛ የሚጠነቀቀው ሐኪማችን (እግዚአብሔር) ይህንን ግዴለሽነታችንና አላስፈላጊ ቅምጥልነትን ፈውሰን ከዓለማዊ ምግባር ወደ መንፈሳዊ ምግባር እንድንገባ ጦም የተባለች መድኃኒትን አዘጋጀልን፡፡
ስለዚህ በበሽታ ምክንያት ራሳቸውን ከምግብ መከልከል ያልቻሉትን እንዲበሉ ነገር ግን ደግሞ ከክፉ ምግባር እንዲጦሙ እመክራቸዋለሁ፡፡ ከምግብ በቀር በሌላው መንፈሳዊ ነገር አብልጠው እንዲተጉ እመክራቸዋለሁ፡፡ በሽተኞች ከምግብ መከልከል ባይችሉም በእውነት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚያስከፍቱ ሌሎች አማራጮች አሉላቸው፡፡ ስለዚህ በሕመም ምክንያት ከምግብ መከልከል ካልተቻላችሁ (ከንስሐ አባቶቻችሁ ጋር በመመካከር) አብዝታችሁ ምጽዋትን ስጡ፤ ከምግብ መከልከል ባትችሉ አብልጣችሁ ጸልዩ፤ ራሳችሁን ከምግብ መከልከል ባትችሉ ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር የተጋችሁ ሁኑ፡፡ በሽታችሁ ይህን ሁሉ ከማድረግ አይከለክላችሁምና… እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ እውነተኛ ጦምን ጡማችኋል፡፡ እግዚአብሔርም ከዚህ የበለጠ ከእናንተ የሚሻው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሐኪማችን ከጥሉላት እንድንከለከል የሚያዘን ፈቃደ ሥጋችን ደክሞ ፈቃደ ነፍሳችን እንዲበረታ በዚያም ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ ነውና…
ስናጠቃልለው በጦም ሰዓታችሁ ይሁን በሌላ ጊዜ ይሁን ሦስት ነገሮችን በሕሊናችሁ ትይዙ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ እነርሱም ክፉ ከመናገር መከልከልን፣ ማንንም ሰው እንደጠላት ከማየት መቆጠብንና፣ እንደ ልምድ አድርጋችሁ ከያዛችሁት መሐላ ትርቁ ዘንድ፡፡ በአጨዳ ላይ ያለ ገበሬ እህሉን ከማሳው በአንዴ እንደማይሰበስብ ነገር ግን በጥቂት በጥቂቱ እንደሚሰበስብ ሁሉ እኛም እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ በዚህ የጦም ወቅት ልንለማመዳቸው እና መልካም ልምዶቻችን ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ እንዲህም በማድረጋችን በቀላሉ መንፈሳዊ ጥበብን ገንዘብ ማድረግ ይቻለናል፡፡ በዚህም ዓለም ሳለን መልካም ተስፋ ያለውን አዝመራ እናፈራለን፡፡ በሚመጣውም ዓለም በክርስቶስ ፊት ያለፍርሃት በደስታ ተሞልተን እንድንቆም ይረዱናል፡፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያበቃንን ጸጋ አግኝተን የክብሩ ወራሾች ያድርገን፡፡

ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ለዓለም ወለዓለም አሜን፡፡

ዘመኑን ዋጁ

ዘመኑን ዋጁ
(በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ምእመናን መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከገለጠላቸው በኋላ አያይዞ እንዴት መኖር እንዳለባቸው መክሮአቸዋል፡፡ ስለመጪው ጊዜ ሲነግራቸው
‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና›› ብሏቸዋል፡፡ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሲመክራቸው ደግሞ ‹‹እንደ ጥበበኞች›› በጥበብ መመላለስ እንደሚገባቸው፤ ዳግመኛም ‹‹በጥንቃቄ›› እና ‹‹በመጠበቅ›› እየኖሩ ዘመኑን እንዲዋጁ አሳስቧቸዋል፡፡ (ኤፌ5.15-16) እነዚህ ቁም ነገሮችለጊዜው በኤፌሶን ላሉ ምእመናን ቢጻፉም ለሁላችን ምክር እናእዝናት የሚሆኑ ናቸውና በየተራ እንመለከታቸዋለን!

‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› ማለት ምን ማለት ነው? የቀን ክፉ አለን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ ክፋት አስቦና ፈቅዶ በሚበድል በሰው ልጅ ዘንድ እንጂ በቀናት ዘንድ ክፋት የለም፡፡ ዕለታትን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ
መልካምነው›› (1ጢሞ4.4) ስለዚህ ዕለታት በሙሉ በተፈጥሮ አንድናቸው፤ እንዲሁም ሁሉም መልካም ናቸው፡፡
የዕለታት መልካቸው የሰው ልጅ ምግባር ነው፡፡ የሰው ሥራ ክፉ የሆነ እንደሆነ ዕለታትም ይከፋሉ፡፡ ሰው መልካም ሲሆን ዘመናቱ መልካም ይሆኑለታል፡፡ ሐዋርያው በዕለት አንጻር የሰውን ክፉነት ሲነግረን ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች›› ናቸው አለን፡፡ በጸሎተ ቤተክርስቲያን ‹‹እግዚኦ አድኅነነ እምዕለት እኪት ወባልሃነ እምኩሉመንሱት›› - ‹‹አቤቱ ከክፉ ቀን ከፈተናም ሁሉ ፈጽመህ አድነን፡፡›› የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ አበው ካህናት ሲያሳርጉ ‹‹ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን!›› የሚሉት እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለ ቃላት መሠረት አድርገው ነው፡፡

የሰውልጅ ምግባር ሲከፋ ዘመናቱ ክፉዎች የሚሆኑት ዕለታት የተፈጠሩት ለሰው ልጆች ጥቅም ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም›› እንዲል፡፡(ማር2.27)

ሐዋርያውም ቀኖች ለሰው የተፈጠሩ መሆናቸውን በሚጠቁም ቃል ‹‹ቀኖቹ›› ማለቱን ልብ እንበል፡፡ ‹‹ቀኖቹ››ያለው የሰው ልጅ ቀኖች ለማለት ነውና፡፡ ስለዚህ ዕለታት ለሰውልጅ መጠቀሚያነት እስከተፈጠሩ ድረስ ሰው ሲያበላሻቸው ይበላሻሉ ማለት ነው፡፡

ሰው ምግባሩን ሲያከፋ ዕለታት እየከፉ የሚሄዱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሰው መልካም ሲሁንም‹‹ቀኖቹ›› መልካም ይሆኑለታል፡፡


መጪው ጊዜ

ነቢዩ ዳንኤል እንደተናገረው ዘመን እየገፋ በሄደ ቁጥር ዕውቀት ይበዛል፡፡ ሥልጣኔም ይሰፋል፡፡ (ዳን12.4) ይሁን እንጂ በሥነ ምግባር ደረጃ የሰው ልጆች ክፋት እየጨመረና በምድር ላይ ኃጢአት በምልዓት እየተፈጸመ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ይህን እውነት በትንቢት መነጽር የተመለከተው ቅዱስ ጳውሎስ

‹‹ቀኖቹ ክፉዎችናቸው›› ማለቱ የሚገባ ነው፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነገር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዘመናት እምነት በሰው ልጅ ዘንድ ጎደሎ እንደሚሆን ‹‹ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?›› ሲል ተናግሯል፡፡(ሉቃ18. )

እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ፍቅርእንደሚቀዘቅዝ ‹‹ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡›› በማለት ከነምክንያቱ አስቀምጦልናል፡፡(ማቴ24.12)

ይህ በግልጥ የሚታይ እውነት ስለሆነ ምስክርም አያስፈልገውም፡፡ እንግዲህ በመጪዎቹ ዘመናት እምነትና ፍቅር በሰው መሃል ካልተገኙ የሰው ልጅ ለበጎ ምግባር ምን መነሻ ይኖረዋል?
ከፍቅርስ የሚበልጥ ምን ምግባር ይኖረዋል?
እንዲህ ስከሆነ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› መባሉ ተገቢ አይደለምን?
ቀኖቹ ክፉዎች መሆናቸው እና የሰው ልጆች መንፈሳዊ ደረጃእየዘቀጠ የሚሄድ መሆኑን ከራሳችን የግል ሕይወት በመነሣት መረዳት የምንችለው ነው፡፡ አብዛኞቻችን ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ትጋት ስንጀምር እንዳነበረን አይሆንልንም፡፡ መንፈሳዊ ኑሮ ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል እንደሚባለው እየሆነብን የምንቸገርብዙዎች ነን፡፡

ስንጀምር የነበረን ለጸሎት ማልዶ መነሣት፣
ዘወትር ቤተክርስቲያን መሄድ፣
በሱባኤ ወራት ወደገዳማት ሄዶ ደጅመጥናት፣
ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣
ቃለ እግዚአብሔርን በመመሰጥና በድስታ ማዳመጥ፣
ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠንቀቅ፣
ንስሐ መግባት፣
ሥጋ ወደሙ መቀበል፣ ወይም
ከመንፈሳዎ ምሥጢራት ስለ መራቃችን መቆጨት
ከውስጣችን ሙጥጥ ብሎ ያለ ይመስላል፡፡

በምትኩ ተስፋ መቁረጥ፣
ድንዛዜ ስንፍና እና
ልዩ ልዩ የኃጢአት ልምምዶች ልባችንን አጣበውታል፡፡ ታዲያ በእኛ ውስጥ የምንመለከተው ይህ ሁኔታ በብዙ ሰዎች ዘንድ መኖሩን በተደጋጋሚ ስንሰማ ዘመኑ እየከፋ መምጣቱን አይነግረንምን?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› በማለት ብቻ አላበቃም፡፡ በሌላ ክፍል ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንደሚመጣ ዕወቅ፡፡›› እያለ መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከነምክንያቱ ጽፏል፡፡ (2ጢሞ3.1)

መጪውጊዜ አስጨናቂ የሚሆነው ሰዎች

‹‹ራሳቸውን የሚውዱ፣ ገንዘብንየሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ቅደስና የሌላቸው፣ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውንየማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ›› ሰለሚሆኑ እንደሆነ አያይዞ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው የቀኖቹን ክፉነት ብቻ ሳይሆን እኛ ከዚህ ሁሉ ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠቁሟልና ያንን ቀጥለን እንመለከታልን፡፡

1ኛ. ዘመኑን መዋጀት
ሐዋርያው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ብሎናል፡፡ዘመንን መዋጀት ማለት ምን ማለት ነው ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመኑን መግዛት፣ ድል ማድረግ፣ ማሸነፍ፣ የራስ ማድረግ፣ ዘመኑን መቅደም እንጂ በዘመን አለመቀደም… ወዘተ ማለት ነው፡፡ዘመን ዘመናት የሚባሉት የሚመጡት አዳዲስ ዓመታት ብቻ አይደሉም፡፡ ያለፈውም ጊዜ የዘመን አካል ነው፡፡ ስለዚህ ዘመንን መዋጀት ስለሚመጣው ብቻ ሳይሆን ስላለፈውም መመርመር፣ ታሪክን በሚገባ ማወቅ፣ ካለፈው መማርና ለወደፊቱ መጠንቀቅ ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ካልመረመርነው ዘመንን ዋጀን አይባልም፡፡የሚመጣውን ብንዋጅ ያለፈውን ዘመን ካልዋጀን ዘመኑን ዋጀን ሊባል አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመን ያፈራውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማወቅና መጠቀም ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም የሚሰፋ ሐሳብ ያለው ነው፡፡
ዘመኑን መዋጀት ማለት በእያንዳንዱ ቀን ፈተናዎችን እንደ የአመጣጣቸው እየለዩ መመልከት ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች ጥንተ ጠላት ሰይጣን ዓለምን ማርኮ ለመግዛት ብዙ አሳሳችመንገዶችን ይጠቀማል፡፡

አዳምንና ሔዋንን የፈተነው አምላክነትን እንዲመኙና ዕፀ በለስን እንዲበሉ በማድረግ ነው፡፡
ኢዮብን የፈተነው ያለውን ሁሉ በማውደም እና በሽታ ላይ እንዲወድቅበማድረግ ነው፡፡
እስራኤልን የወርቅ ጥጃ እንዲያመልኩ ስቧቸዋል፡፡

ክብር ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ የፈተናው መንገድ ግን ከተዘረዘሩት በእጅጉ ይለያል፡፡ ስለዚህ ሰይጣን የሚፈትነን እንደዘመናችን ስለሆነ ዘመኑን ካልዋጀን ፈተናውን ማለፍ አንችልም፡፡ስለዚህ ሐዋርያው እንደመከረን ‹‹መጠንቀቅና›› ራሳችንን ‹‹መጠበቅ››አለብን፡፡ ‹‹መጠንቀቅ›› ካላወቅነው፤ ነገር ግን ሊሆን ይችላል ብለን ከምንገምተው ክፉ ነገር ሁሉ ራስን ለማዳን መሽቀዳደምሲሆን ‹‹መጠበቅ›› ደግሞ ክፉ መሆኑን ከተረዳነው ነገር ሁሉእንዳይጎዳን የምናደርገውን ጥረት ያመለክታል፡፡ (ኤፌ5፦5)

2ኛ. በጥበብ መመላለስ
ጥበብ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ይመደባል፡፡ ወይም በቅዱስ ያዕቆብ ገለጻ መሠረት ሰማያዊ እና ምድራዊ ጥበብ ይባላል፡፡ (ያዕ3.15-17)

የመንፈሳዊ ጥበብ መነሻው ሃይማኖትነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ

‹‹የጥበብ መጀመሪያእግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ይላልና፡፡(መዝ1)0፥0)

እግዚአብሔርን መፍራት ደግሞ በሃይማኖትይተረጎማል፡፡ ምክንያቱም በዓይነ ሥጋ ያላዩትን እግዚአብሔርን ኃጢአት ብሠራ ይፈርድብኛል ብሎ መፍራት ራሱ ሃይማኖት ነውና፡፡ ስለዚህ የጥበብ መጀመሪያ ሃይማኖት መሆኑን በዚህ እናውቃለን፡፡ እንዲህ ከሆነ በጥበብ መመላለስ ማለት ደግሞበሃይማኖት መመላለስ ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም በጥበብ መመላለስ ማለት በዚህች ዓለም ማታለልና ክፉ አሠራር እንዳይያዙ በዘዴ፣ በዕውቀት፣ በማስተዋል፣በብልሃትና በፈሊጥ መመላለስ ማለት ነው፡፡
በሃይማኖት መመላለስ ከክፉ ሁሉ ይሰውራል፡፡ እውነተኛ የልብ እምነት ክፉውን ሁሉ ይመክታል፡፡ ‹‹ዓለምንም የሚያሸንፈውእምነታችን ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ ሃይማኖት ያለው ሰው በምንም በማንም አይሸነፍም፡፡ (1ዮሐ5፥4)

ስለዚህ በዚህ ዘመን ሃይማኖታችንን ጠበቅ አድርገን መያዛችን ለአሸናፊነታችን ዋስትናነው፡፡


3ኛ. ከክፉ መሸሽ

አብዛኞቻችን በጎ ዘመን ላይ ደርሰን በሰላምና በደስታ ለመኖር የምንጓጓውን ያህል ለዚህ የሚያበቃውን መስፈርት ግን ለማሟላት ስንደክም አንገኝም፡፡ ወደፊት በመልካም ለመኖርየሚጠበቅብን ነገር አለ፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን ልብ እንበል፡፡

አስቀድሞ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው? በጎንምዘመን ለማየት የሚወደድ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ መቼም ለዚህ ጥያቄ እኔ እፈልጋለው ብሎ መልስ የማይሰጥ አይኖርም፡፡ ቀጥሎ ማሟላት የሚገባን ነገር መኖሩን ‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል፡፡ከንፈሮችህም ሽንገላን ሽንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካምንምአድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም›› ሲል ይጠቁመናል፡፡(መዝ33.12-14) ስለዚህ በአጭሩ ከክፉ መሸሽና መልካምማድረግ የወደፊት መንገዳችንን እና መጪውን ዘመን ብሩህ ያደርግልናል፡፡ መልካም አኗኗር ከውስጣችን የሚፈልቅ እንጂ በግዢ የሚገኝ ቁስ አይደለምና፡፡ ደስተኛና ሰላማዊ ኑሮ መኖር ከፈለግን ምግባራችንን እናስተካክል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ

‹‹መልካምብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን?›› ብሎአልና፡፡ (ዘፍ4.7) መልካም ከሠራን ፊታችን ይበራል፡፡ ዘመኑም መልካምይሆንልናል፡፡ እንጂ መልካም አዲስ አመት ስለተባባልን ብቻዘመኑ መልካም እንደማይሆንልን እንረዳ! በጎ መመኘታችንእንደተጠበቀ ሆኑ በጎ ለመሥራት አሁኑኑ እንነሣ!

ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን!አሜን!
Photo: ዘመኑን ዋጁ (በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ምእመናን መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከገለጠላቸው በኋላ አያይዞ እንዴት መኖር እንዳለባቸው መክሮአቸዋል፡፡ ስለመጪው ጊዜ ሲነግራቸው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና›› ብሏቸዋል፡፡ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሲመክራቸው ደግሞ ‹‹እንደ ጥበበኞች›› በጥበብ መመላለስ እንደሚገባቸው፤ ዳግመኛም ‹‹በጥንቃቄ›› እና ‹‹በመጠበቅ›› እየኖሩ ዘመኑን እንዲዋጁ አሳስቧቸዋል፡፡ (ኤፌ5.15-16) እነዚህ ቁም ነገሮችለጊዜው በኤፌሶን ላሉ ምእመናን ቢጻፉም ለሁላችን ምክር እናእዝናት የሚሆኑ ናቸውና በየተራ እንመለከታቸዋለን! ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› ማለት ምን ማለት ነው? የቀን ክፉ አለን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ ክፋት አስቦና ፈቅዶ በሚበድል በሰው ልጅ ዘንድ እንጂ በቀናት ዘንድ ክፋት የለም፡፡ ዕለታትን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካምነው›› (1ጢሞ4.4) ስለዚህ ዕለታት በሙሉ በተፈጥሮ አንድናቸው፤ እንዲሁም ሁሉም መልካም ናቸው፡፡ የዕለታት መልካቸው የሰው ልጅ ምግባር ነው፡፡ የሰው ሥራ ክፉ የሆነ እንደሆነ ዕለታትም ይከፋሉ፡፡ ሰው መልካም ሲሆን ዘመናቱ መልካም ይሆኑለታል፡፡ ሐዋርያው በዕለት አንጻር የሰውን ክፉነት ሲነግረን ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች›› ናቸው አለን፡፡ በጸሎተ ቤተክርስቲያን ‹‹እግዚኦ አድኅነነ እምዕለት እኪት ወባልሃነ እምኩሉመንሱት›› - ‹‹አቤቱ ከክፉ ቀን ከፈተናም ሁሉ ፈጽመህ አድነን፡፡›› የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ አበው ካህናት ሲያሳርጉ ‹‹ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን!›› የሚሉት እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለ ቃላት መሠረት አድርገው ነው፡፡ የሰውልጅ ምግባር ሲከፋ ዘመናቱ ክፉዎች የሚሆኑት ዕለታት የተፈጠሩት ለሰው ልጆች ጥቅም ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም›› እንዲል፡፡(ማር2.27) ሐዋርያውም ቀኖች ለሰው የተፈጠሩ መሆናቸውን በሚጠቁም ቃል ‹‹ቀኖቹ›› ማለቱን ልብ እንበል፡፡ ‹‹ቀኖቹ››ያለው የሰው ልጅ ቀኖች ለማለት ነውና፡፡ ስለዚህ ዕለታት ለሰውልጅ መጠቀሚያነት እስከተፈጠሩ ድረስ ሰው ሲያበላሻቸው ይበላሻሉ ማለት ነው፡፡ ሰው ምግባሩን ሲያከፋ ዕለታት እየከፉ የሚሄዱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሰው መልካም ሲሁንም‹‹ቀኖቹ›› መልካም ይሆኑለታል፡፡ መጪው ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል እንደተናገረው ዘመን እየገፋ በሄደ ቁጥር ዕውቀት ይበዛል፡፡ ሥልጣኔም ይሰፋል፡፡ (ዳን12.4) ይሁን እንጂ በሥነ ምግባር ደረጃ የሰው ልጆች ክፋት እየጨመረና በምድር ላይ ኃጢአት በምልዓት እየተፈጸመ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ይህን እውነት በትንቢት መነጽር የተመለከተው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎችናቸው›› ማለቱ የሚገባ ነው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነገር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዘመናት እምነት በሰው ልጅ ዘንድ ጎደሎ እንደሚሆን ‹‹ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?›› ሲል ተናግሯል፡፡(ሉቃ18. ) እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ፍቅርእንደሚቀዘቅዝ ‹‹ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡›› በማለት ከነምክንያቱ አስቀምጦልናል፡፡(ማቴ24.12) ይህ በግልጥ የሚታይ እውነት ስለሆነ ምስክርም አያስፈልገውም፡፡ እንግዲህ በመጪዎቹ ዘመናት እምነትና ፍቅር በሰው መሃል ካልተገኙ የሰው ልጅ ለበጎ ምግባር ምን መነሻ ይኖረዋል? ከፍቅርስ የሚበልጥ ምን ምግባር ይኖረዋል? እንዲህ ስከሆነ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› መባሉ ተገቢ አይደለምን? ቀኖቹ ክፉዎች መሆናቸው እና የሰው ልጆች መንፈሳዊ ደረጃእየዘቀጠ የሚሄድ መሆኑን ከራሳችን የግል ሕይወት በመነሣት መረዳት የምንችለው ነው፡፡ አብዛኞቻችን ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ትጋት ስንጀምር እንዳነበረን አይሆንልንም፡፡ መንፈሳዊ ኑሮ ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል እንደሚባለው እየሆነብን የምንቸገርብዙዎች ነን፡፡ ስንጀምር የነበረን ለጸሎት ማልዶ መነሣት፣ ዘወትር ቤተክርስቲያን መሄድ፣ በሱባኤ ወራት ወደገዳማት ሄዶ ደጅመጥናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ ቃለ እግዚአብሔርን በመመሰጥና በድስታ ማዳመጥ፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠንቀቅ፣ ንስሐ መግባት፣ ሥጋ ወደሙ መቀበል፣ ወይም ከመንፈሳዎ ምሥጢራት ስለ መራቃችን መቆጨት ከውስጣችን ሙጥጥ ብሎ ያለ ይመስላል፡፡ በምትኩ ተስፋ መቁረጥ፣ ድንዛዜ ስንፍና እና ልዩ ልዩ የኃጢአት ልምምዶች ልባችንን አጣበውታል፡፡ ታዲያ በእኛ ውስጥ የምንመለከተው ይህ ሁኔታ በብዙ ሰዎች ዘንድ መኖሩን በተደጋጋሚ ስንሰማ ዘመኑ እየከፋ መምጣቱን አይነግረንምን? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› በማለት ብቻ አላበቃም፡፡ በሌላ ክፍል ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንደሚመጣ ዕወቅ፡፡›› እያለ መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከነምክንያቱ ጽፏል፡፡ (2ጢሞ3.1) መጪውጊዜ አስጨናቂ የሚሆነው ሰዎች ‹‹ራሳቸውን የሚውዱ፣ ገንዘብንየሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ቅደስና የሌላቸው፣ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውንየማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ›› ሰለሚሆኑ እንደሆነ አያይዞ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው የቀኖቹን ክፉነት ብቻ ሳይሆን እኛ ከዚህ ሁሉ ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠቁሟልና ያንን ቀጥለን እንመለከታልን፡፡ 1ኛ. ዘመኑን መዋጀት ሐዋርያው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ብሎናል፡፡ዘመንን መዋጀት ማለት ምን ማለት ነው ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመኑን መግዛት፣ ድል ማድረግ፣ ማሸነፍ፣ የራስ ማድረግ፣ ዘመኑን መቅደም እንጂ በዘመን አለመቀደም… ወዘተ ማለት ነው፡፡ዘመን ዘመናት የሚባሉት የሚመጡት አዳዲስ ዓመታት ብቻ አይደሉም፡፡ ያለፈውም ጊዜ የዘመን አካል ነው፡፡ ስለዚህ ዘመንን መዋጀት ስለሚመጣው ብቻ ሳይሆን ስላለፈውም መመርመር፣ ታሪክን በሚገባ ማወቅ፣ ካለፈው መማርና ለወደፊቱ መጠንቀቅ ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ካልመረመርነው ዘመንን ዋጀን አይባልም፡፡የሚመጣውን ብንዋጅ ያለፈውን ዘመን ካልዋጀን ዘመኑን ዋጀን ሊባል አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመን ያፈራውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማወቅና መጠቀም ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም የሚሰፋ ሐሳብ ያለው ነው፡፡ ዘመኑን መዋጀት ማለት በእያንዳንዱ ቀን ፈተናዎችን እንደ የአመጣጣቸው እየለዩ መመልከት ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች ጥንተ ጠላት ሰይጣን ዓለምን ማርኮ ለመግዛት ብዙ አሳሳችመንገዶችን ይጠቀማል፡፡ አዳምንና ሔዋንን የፈተነው አምላክነትን እንዲመኙና ዕፀ በለስን እንዲበሉ በማድረግ ነው፡፡ ኢዮብን የፈተነው ያለውን ሁሉ በማውደም እና በሽታ ላይ እንዲወድቅበማድረግ ነው፡፡ እስራኤልን የወርቅ ጥጃ እንዲያመልኩ ስቧቸዋል፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ የፈተናው መንገድ ግን ከተዘረዘሩት በእጅጉ ይለያል፡፡ ስለዚህ ሰይጣን የሚፈትነን እንደዘመናችን ስለሆነ ዘመኑን ካልዋጀን ፈተናውን ማለፍ አንችልም፡፡ስለዚህ ሐዋርያው እንደመከረን ‹‹መጠንቀቅና›› ራሳችንን ‹‹መጠበቅ››አለብን፡፡ ‹‹መጠንቀቅ›› ካላወቅነው፤ ነገር ግን ሊሆን ይችላል ብለን ከምንገምተው ክፉ ነገር ሁሉ ራስን ለማዳን መሽቀዳደምሲሆን ‹‹መጠበቅ›› ደግሞ ክፉ መሆኑን ከተረዳነው ነገር ሁሉእንዳይጎዳን የምናደርገውን ጥረት ያመለክታል፡፡ (ኤፌ5፦5) 2ኛ. በጥበብ መመላለስ ጥበብ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ይመደባል፡፡ ወይም በቅዱስ ያዕቆብ ገለጻ መሠረት ሰማያዊ እና ምድራዊ ጥበብ ይባላል፡፡ (ያዕ3.15-17) የመንፈሳዊ ጥበብ መነሻው ሃይማኖትነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የጥበብ መጀመሪያእግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ይላልና፡፡(መዝ1)0፥0) እግዚአብሔርን መፍራት ደግሞ በሃይማኖትይተረጎማል፡፡ ምክንያቱም በዓይነ ሥጋ ያላዩትን እግዚአብሔርን ኃጢአት ብሠራ ይፈርድብኛል ብሎ መፍራት ራሱ ሃይማኖት ነውና፡፡ ስለዚህ የጥበብ መጀመሪያ ሃይማኖት መሆኑን በዚህ እናውቃለን፡፡ እንዲህ ከሆነ በጥበብ መመላለስ ማለት ደግሞበሃይማኖት መመላለስ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም በጥበብ መመላለስ ማለት በዚህች ዓለም ማታለልና ክፉ አሠራር እንዳይያዙ በዘዴ፣ በዕውቀት፣ በማስተዋል፣በብልሃትና በፈሊጥ መመላለስ ማለት ነው፡፡ በሃይማኖት መመላለስ ከክፉ ሁሉ ይሰውራል፡፡ እውነተኛ የልብ እምነት ክፉውን ሁሉ ይመክታል፡፡ ‹‹ዓለምንም የሚያሸንፈውእምነታችን ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ ሃይማኖት ያለው ሰው በምንም በማንም አይሸነፍም፡፡ (1ዮሐ5፥4) ስለዚህ በዚህ ዘመን ሃይማኖታችንን ጠበቅ አድርገን መያዛችን ለአሸናፊነታችን ዋስትናነው፡፡ 3ኛ. ከክፉ መሸሽ አብዛኞቻችን በጎ ዘመን ላይ ደርሰን በሰላምና በደስታ ለመኖር የምንጓጓውን ያህል ለዚህ የሚያበቃውን መስፈርት ግን ለማሟላት ስንደክም አንገኝም፡፡ ወደፊት በመልካም ለመኖርየሚጠበቅብን ነገር አለ፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን ልብ እንበል፡፡ አስቀድሞ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው? በጎንምዘመን ለማየት የሚወደድ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ መቼም ለዚህ ጥያቄ እኔ እፈልጋለው ብሎ መልስ የማይሰጥ አይኖርም፡፡ ቀጥሎ ማሟላት የሚገባን ነገር መኖሩን ‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል፡፡ከንፈሮችህም ሽንገላን ሽንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካምንምአድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም›› ሲል ይጠቁመናል፡፡(መዝ33.12-14) ስለዚህ በአጭሩ ከክፉ መሸሽና መልካምማድረግ የወደፊት መንገዳችንን እና መጪውን ዘመን ብሩህ ያደርግልናል፡፡ መልካም አኗኗር ከውስጣችን የሚፈልቅ እንጂ በግዢ የሚገኝ ቁስ አይደለምና፡፡ ደስተኛና ሰላማዊ ኑሮ መኖር ከፈለግን ምግባራችንን እናስተካክል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መልካምብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን?›› ብሎአልና፡፡ (ዘፍ4.7) መልካም ከሠራን ፊታችን ይበራል፡፡ ዘመኑም መልካምይሆንልናል፡፡ እንጂ መልካም አዲስ አመት ስለተባባልን ብቻዘመኑ መልካም እንደማይሆንልን እንረዳ! በጎ መመኘታችንእንደተጠበቀ ሆኑ በጎ ለመሥራት አሁኑኑ እንነሣ! ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን!አሜን!

ምክረ አበው

ምክረ አበው

“ልጆቼ! ሓኪሞች ብትሆኑ፣
መሀንዲሶች ብትሆኑ፣
የሽመና ሠራተኞች ብትሆኑ፣
መርከበኞችም ብትሆኑ መልካም ነው፡፡

ይህን ጥበብ መማራችሁም ጥሩ ነው፡፡

እኔ ግን ከዚህ የበለጠ ጥበብ አሳያችኋለሁ፡፡

በዚህ (በተማራችሁት ምድራዊ) ጥበባችሁም ሌላ ጥበብ ትማሩበት ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡

ሰማያዊን ጥበብ! ከላይ በገልጽኩላችሁና እናንተ በተማራችሁት ጥበብ ተጠቅማችሁ
ገንዘብ ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡ በዚህ ገንዘባችሁ ግን ድሆችን መርዳት ልመዱበት፡፡
ይህ የምነግራችሁን ጥበብ እንደ ቀላል የምታዩት አትሁኑ፡፡

መሀንዲሶች ብትሆኑ በምህንድስና ጥበባችሁና እውቀታችሁ በዚህ ምድር የሚያማምሩ ቪላ ቤቶችን ልትሠሩ ትችላላችሁ፡፡

በምነግራችሁ ጥበብ ግን
በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ የዘላለም ቤታችሁን ትሠራላችሁ፡፡

በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤታችሁ በጣም ብዙ ወጪ ብዙም ድካም ይጠይቃችኋል፡፡

በምነግራችሁ ጥበብ ግን ብዙ ልፋት የለውም፡፡

ወጪአችሁ መልካምና ፈቃደኛ መሆን ብቻ ነው፡፡

በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤት የተለያዩ ዓይነት ብረቶችና ማቅለጫዎች

እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን ትጠቀማላችሁ፡፡

በምነግራችሁ ጥበብ ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋችሁም፡፡

የሚያስፈልጋችሁ ብሎን ወይንም ብረት ወይንም የከበረ ድንጋይ ሳይሆን መልካም ምግባራችሁና በጎ ፈቃዳችሁ ብቻ ነው፡፡

እንደውም እኔ እነዚህ የተማራችኋቸው ጥበቦች ጥበብ ብዬ ለመጥራት በጣም እቸገራለሁ፡፡
ለምን ብትሉኝ ከምነግራችሁ ጥበብ ጋር ሳወዳድራቸው በጣም ስለሚያንሱብኝ አያያዛቸው ላላወቀበት ሰውም ብዙ ጉዳት ስለሚያመጡ፡፡

እስኪ አስተውሉት! አንድ ሰው በዚህ ምድር ባገኘው ጥበብና ገንዘብ ተጠቅሞ ድሆችን መርዳት ሲገባው አላግባብ ሲበላ ሲጠጣ በኋላ ግን በስኳር፣ በሪህ፣ በቁርጥማት፣ በራስ ምታት፣ በልብና በኩላሊት በሽታ የሚሰቃይ ከሆነ ይህ ጥበብ እለው ዘንድ እንዴት እደፍራለሁ? እንግዲያውስ ጥበባችሁ ጥበብ ይሁንላችሁ፡፡ ጥበባችሁ ለሥጋችሁም ለነፍሳችሁም የሚጠቅም እንጂ በዚህ ዓለምም ይሁን በሚመጣው ዓለም የሚጎዳችሁ አይሁን፡፡ ” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
2

ጳጉሜ

ጳጉሜ/ጳጉሜን/
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከነሐሴ በኋላ ጳጉሜን የምትባል አምስት ቀን አለች፡፡

ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፡፡

ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ኾናለች፡፡

ጳጉሜን የሚለው ስያሜዋ ግን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ መኾኑ በአበው ቃል ተነግሯል፡፡
“ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው ፡፡

በግእዝ ቋንቋችን ተውሳክ ማለት ነው፡፡

ተውሳክ ማለት ተጨማሪ ማለት ነው፡፡

“ወሰከ - ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ኤውሮፓዎች ጳጉሜን የወር ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጠር ሠላሳ ስናደርግ እነርሱ ሠላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከነሱ ብለው ደምረውታል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡

ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፡-2-7፡፡

እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ 8፡-2 ፡፡

ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡

ሊቃውንቱ እንደ ሱባኤ ቀን ቀኖና እንዲፈጽምባት ለብቻ ለይተው አኑረውታል፡፡ “ይህ ዓለም ኑሮ፣ ኑሮ በመጨረሻ ያልፋል፡፡ ጌታ ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል” ሲሉ የገታ የመምጣቱ ነገር እንዲነገርባት፣ መሥዋዕት እንዲሠዋባት፣ ጾም እንዲያዝባት፣ ምጽዋት እንዲመጸወትባት ለይተው መድበዋታል፡፡
ሕዝቡ ሳይቀር “ጳጉሜን ዕድሜ ትሰጠናለች፤ በኋላም ታድነናለች” ብለው ጾም ይጾሙባታል፡፡ የዚሁም ማስረጃ በቅዱስ መልከ ጸዴቅ ድርሳን ይገኛል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ የጾም ሥርዐት ይፈጽሙባት ነበር፡፡ ሌሎችም ሽማግሌዎችና ባልቴቶች አክብረው ይጾሙባታል፡፡ ኾኖም የጳጉሜን አቆጣጠር አንዱ ከወር ጋራ፣ ሌላውም ከዓመት ጋራ ቢያደርገውም በሀሉም አቆጣጠር ውስጥ ሕያዊት ኾና መገኘቷ የታወቀ ነው፡፡

የነቢዩ ኄኖክ መጽሐፍም ጳጉሜን ጨርሶ አልዘነጋትም፡፡
ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ጷጉሜ) ይሁንላችሁ፡፡

ከንቲባው

ለመለወጥ ጥረት ስለምታደርግ ነፍስ አባ ዮሐንስ ሐጺር ለአንድ መነኰሴ ያስተማረበት ምሳሌ

እንደሚከተለው ተጽፎ ይገኛል፡-“በከተማ መካከል ብዙ ወዳጆች ያሏት አንዲት ቆንጆ ሴተኛ አዳሪ ነበረች፡፡

የከተማዋ ከንቲባ ወደ እርሷ ቀርቦ፡- መልካም ሴት እንደምትሆኚ ቃል ከገባሽልኝ አሁኑኑ አገባሻለሁ ይላታል፡፡

እርሷም በሐሳቡ ተስማምታ ቃል ስለገባችለት ወደ ቤቱ ይዟት ሄደ፡፡

ወዳጆቿ ድጋሚ ሊያገኟት ስለ ፈለጉ እንዲህ እያሉ ይመካከሩ ነበር፡- የከተማው ከንቲባ ወዳጃችንን ወደ ቤቱ ወስዷታል፡፡

በግልጽ ወደ ቤቱ ከሄድን ስለሚያውቅብንና ስለሚያስፈርድብን በቤቱ ጓሮ ዞረን እናፏጭላት፡፡ የፉጨታችንን ድምጽ ለይታ ስለምታውቃቸው ከቤቷ ወርዳ ትመጣለች፡፡ ለማንኛውም ግን እርሷ ትምጣልን እንጂ እኛ አንጣላም አሉ፡፡

በመጨረሻ እንደተመካከሩት በቤቱ ጓሮ ዞረው ሲያፏጩላት ጀሮዎቿ ቆሙ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ ልትወርድ ስላልፈለገች ፈጠን ብላ ወደ እንግዳ መቀበያው አዳራሽ ገባችና በሮቿን ዘጋግታ ከውስጥ ተቀመጠች፡፡

ልክ እንደዚሁ ነፍሳችን በዚህች ሴት ስትመሰል ወዳጆቿ ደግሞ ምኞቶቻችን ይመስላሉ፡፡

ከንቲባው የሚመሰለው በምንወደው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

በቤቱ ውስጥ ያለው የእንግዳ መቀበያ አዳራሽ በዘላለማዊ ቤታችን ወይም በመንግሥተ ሰማያት ሲመሰል

የሚያፋጩላት ሰዎች ደግሞ በርኩሳን መናፍስት ይመሰላሉ፡፡

በመጨረሻም ይህን ምሳሌ ነፍሳችን ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ከተጠጋች በእርሱ ኃይል እንደምትኖር ያስረዳናል፡፡”

እግዚአብሔር አምላክ አስተዋይ ልቦና ያድለን አሜን !!!

ክርስቲያናዊ አለባበስ

ክርስቲያናዊ አለባበስ

“ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ወንድም የሴትን ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፡፡” ዘዳ. 22፡5

ስለ አለባበሳችን እንወያያለን ዛሬም እህቶቻችን ላይ እናተኩራለን አበዛኸው ምነው እኛን ብቻ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለው፡፡

ስለ አለባበስ መነጋገር ያስፈለገን እውነተኛ ክርስቲያን በአነጋገሩ፣ በአረማመዱ፣ በአመጋገቡ፣ በአለባበሱ፣ ብቻ በሁሉ ነገሩ የተለየ መሆን ስላለበት ነው ይኸውም ሁሉን በአግባብና በሥርዓት ስለማድረግ ነው እህቶቻችን ላይ ማተኮር ያስፈለገው ደግሞ በአብዛኛው በዚህ ረገድ ትችት የሚበዛው እነሱ ላይ ስለሆነ ነው፡፡

እነሆ ውድድሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረና እየከፋ ነው ለመልካም ነገር መወዳደር ባልከፋ ነገር ግን በከተማችን በተለይም በዋና ዋና መንገዶች ላይ የምናየው የእህቶቻችን አለባበስ አንዷ ከሌላዋ ልቃና በልጣ ለመታየት የሚደረግ ግብግብ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ በእርግጥ እህቶቻችን በዚህ እንደማይስማሙ እናውቃለን አብዛኞቹም ስለተመቸኝና የምወደው አይነት አለባበስ ስለሆነ ነው እንዲህ የምለብሰው ይሉናል ይሁን እንጂ እውነታው ሌላ ይመስላል ምክንያቱም:-
* ብርድልብስ ለብሰን እንኳን በማንቋቋመው የብርድ ወቅት ሰውነትን በቅጡ የማይሸፍን ብጣሽ ጨርቅ ጣል አድርጎ መውጣት እንዴት ያለ ምቾት ነው?

*እጅግ አስጨናቂ ሙቀት ባለበት ሰዓት ሰውነት ላይ ተጣብቆ ሌላ ጭንቀት የሚፈጥር አለባበስ እንደምን ብሎ ያስደስታል?

ዓላማችን ምንም ይሁን እሱ ላይ የመከራከር ፍላጎት የለንም ነገር ግን አለባበሳችንን እንደ ክርስቲያን እንፈትሸው ዘንድ ይገባልና ይህ ተፃፈ

መሰልጠን ወይስ መሰይጠን?

አብዛኞቹ ሴቶች ይህን ተግባር ስልጣኔ እንጂ ስህተት ነው ብለው አያምኑም፡፡ ለነዚህ ሴቶች ከኃይማኖት ብቻ ሳይሆን ከባህላችን ጭምር ያፈነገጠውን የምዕራባውያን አለባበስ መልበስ ዘመናዊነት ነው፡፡ ላንቺስ? መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል?
-----------------------------------------/////////////////////////------------------------------------

ማንኛዋም ሴት የሰውነቷን ቅርፅ የሚያሳይ ወይም ክፍትፍት ልብስ ለብሳ መሄዷ የሁሉንም ወንዶች ስሜት መፈታተኗ እርግጥ ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ህይወት ደካማ የሆኑትን ደግሞ ለኃጢያት አጋልጦ ይሰጣል፡፡ እዚህ ላይ የተሳሳተው በራሱ ደካማነት ነው ብሎ ምክንያት መስጠት አይቻልም እግዚአብሔር የሚጠይቀው በማን ተሰናከለ የሚለውን ጭምር ነውና በክርስትና ደግሞ ሰውን ማሰናከል እጅግ የከፋ ኃጢያት ነው፡-

“ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባህር መስጠም ይሻለው ነበር፡፡” ማቴ. 18፡6

አንዳንድ ሴቶች እግዚአብሔር ምን ሰራሽ እንጂ ምን ለበስሽ አይለኝም ይላሉ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል

“እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለው፡፡” ትን.ሶፎ. 1፡18

እንግዲህ የሴቶቹን እንቀበል ወይስ የእግዚአብሔርን ምርጫው ያንቺው ነው እህቴ መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል፡- “ከስው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡” የሐዋ. 5፡29

በሴቶችና በወንዶች መካከል የአለባበስ ልዩነት ሊኖር ይገባል

“ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ወንድም የሴትን ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፡፡” ዘዳ. 22፡5

ታዲያ ቀሚስን የወንድ ሱሪን የሴት ማን አደረገው? ይህ የሰነፍና ለስህተታቸው ምክንያትን የሚሹ ሴቶች የሚያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ኦርቶዶክሳውያን የእግዚአብሔርን ቃል አውቀን ልንፈፅመው እንጂ በቃሉ ላይ የምንፍቅና ጥያቄ እናነሳ ዘንድ ተገቢ አይደለም ግን ደግሞ ተፈጥሯችንን ብቻ በማየት ህሊናችን እራሱ ቢናገር ሱሪ የሴት ነውን? ቀሚስስ የወንድ ነው እንዴ “ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁምን? 1ኛ ቆሮ. 11፡14

“ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም፡፡” 1ኛ. ቆሮ. 11፡16

ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ስህተት መሆኑን መናገር እንጂ መከራከር አያስፈልግም ክርስትና በምርጫ ነውና፡፡

“በፊትህ እሳትና ውሃን አኑሬአለው ወደ ወደድከው እጅህ ክተት፡፡” ሲራ. 15፡15

እዚህ ላይ ግን ቀሚስ ሲባል ከውስጥ ሱሪ የማይሻለውን ብጣሽ ጨርቅ እንዲሁም ቁመቱ ረዥም ሆኖ ከሰውነት ጋር የሚጣበቀውን አይነት አለባበስ ማለት እንዳልሆነ ልብ እንበል፡፡

እህቶቻችን ሆይ ማስተዋልን ትላበሱ ዘንድ እንለምናችኋለን መሰልጠንና መሰይጠንም ትለዩ ዘንድ ይሁን ሰውነትሽ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነውና ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጊለት፡፡

ደግሞም ክርስትና ራስ ወዳድነትን አብዝታ ትጠላለች ምንም ነገር ስናደርግ ስለ ሌላው ሰው ልናስብ ያስፈልገናል እኛስ ሰውን ወደ ዝሙት ሊያመራው ስለሚችል አለባበሳችን እጅግ ተጨነቅን ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ ወንድማችንን ስለማሰናከል ምን አለ

“መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም፡፡” 1ኛ.ቆሮ 8፡13

እንግዲህ ክርስትና እዚህ ድረስ ነው ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለ ወንድሞችና እህቶቻችን የምናስብባት ለእነሱም መሰናከያ እንዳንሆን እየተጠነቀቅን ሁሉን በአግባብና በሥርዓት የምናደርግባት፤ እምነታችንን በምግባር የምንገልጽባት ናት፡፡

“በእውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን፡፡ ትን.ኤር. 13፡27

እህቴ ሆይ አንቺም ኤርሚያስ እንዳለው ኢትዮጵያዊነትሽን ጠብቂ የምዕራባውያን በዓል ከሆነው አለባበስም ሆነ የምንዝር ጌጥ ራስሽን አርቀሽ በሚያኮራው ኢትየጵያዊ ባህላችን ትዋቢ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳሽ፡፡

ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡ አሜን!!!!

ሁላችን ምግባር ያለው እምነት እንዲኖረን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን!!!

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ!!!

በብሉይ ኪዳን ስሞች ትርጓሜያቸው

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካሉ ስሞች ከነትርጓሜያቸው በጥቂቱ

1. ዮሐንስ ፡- የእግዚአብሔር ፀጋ (ሀሴት፣ ፍስሀ)
2. ዳንኤል ፡- እግዚአብሔር ፈራጅ ነው
3. ኤልሳዕ ፡- እግዚአብሔር ደህንነት
4. አሞን ፡- የወገኔ ልጅ
5. እስራኤል ፡- የእግዚአብሔር ህዝቦች
6. ማርያም ፡- የእግዚአብሔር ስጦታ
7. ሀና ፡- ፀጋ
8. ሩሀማ ፡- ምህረት የሚገባት
9. ኢያሱ ፡- እግዚአብሔር አዳኝ ነው፣ መድሃኒት
10. ጌርሳም፡- ከሌላ ምድር ስደተኛ ነኝ
11. እዮሳፍጥ፡- እግዚአብሔር ፈርዷል
12. እዮአም ፡- አዳኝ
13. ኢዮሲያስ፡- ከፍ ከፍ አለ
14. ኤልሳቤጥ፡- እግዚአብሔር መሀላዬ ነው
15. አብርሃም ፡- የብዙሃን አባት
16. ኢሊዲያ (ይድድያ)፡- በእግዚአብሔር የተወደደ
17. ኤዶንያስ ፡- እግዚአብሔር ጌታዬ ነው
18. ኦዶኒራም ፡- ጌታየ ከፍ ያለ ነው አለ
19. ሆሴዕ፡- እግዚአብሔር መድኃኒት ነው
20. ሕዝቅያዝ ፡- እግዚአብሔር ሀይሌ ነው
21. ጴጥሮስ፡- መሰረት
22. ሴት ፡- ምትክ
23. ሙኤል ፡- እግዚአብሔርን ለምኜዋለው
24. አቤል ፡- የህይወት እስትንፋስ
25. ጎዶሊያስ ፡- እግዚአብሔር ታላቅ ነው
26. ስጥና ፡- ተዘጋ
27. ማቴዎስ ፡- ሞገስ
28. ፌቨን፡- የእግዚአብሔር አገልጋይ
29. ሚኪያስ ፡- እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን አለ
30. ይሁዳ፡- አማኝ (የአማኝ ልጅ)
31. ወንጌል ፡- የምስራች
32. ኤርሚያስ ፡- እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርጋል
33. ህዝቅኤል ፡- እግዚአብሔር ብርታት ይሰጣል
34. ማራናታ፡- እግዚአብሔር ቶሎ ና
35. ሆሴዕ ፡- እግዚአብሔር ያድናል
36. አሞፅ ፡- ሀይል
37. ኤሴቅ ፡- የተጣላሁብሽ
38. ሚኪያስ ፡- እግዚአብሔር የሚመስል ማን ነው
39. ኢዮኤል፡- እግዚአብሔር አምላክነው
40. አብድዩ፡- የእግዚአብሔር አገልጋይ
41. ዮናስ ፡- ርግብ (የዋህ፣እሩሩህ)
42. እምባቆም ፡- እቅፍ
43. ሶፎኒያስ ፡- እግዚአብሔር ጠብቋል
44. ሀጌ፡- በሀላዊ ወይም በበዓል የተወለደ
45. ዘካርያስ ፡- እግዚአብሔር ያስታውሳል
46. ሚልክያስ ፡- መልክተኛዬ
47. ናታኔም ፡- የእግዚአብሔር ጠራጊ
48. አቤኔዘር ፡- ምስጋናዬን ለእግዚአብሔር አቀርባለው

ዮሐንስ በሥነ-ፍጥረት መመስሉ

ዮሐንስ በሥነ-ፍጥረት መመስሉ

1 ከአራቱ ኪሩቤል በገጸ ንሰር ይመሰላል ምክንያቱም፡-

❉ ንስር በእግሩ ይሸከረከራል በክንፉም ይበራል
ዮሐንስም ቀዳሚሁ ብሎ ሰማያዊን
ሥጋ ኮነ ብሎ ምድራዊ ልደቱን ጽፏልና

❉ ንሰር ከፍብሎ እንዲበር
ዮሐንስም ምሰጢረ መለኮት ተገልጦለት
ቀዳሚሁ ቃል…ብሎ ጽፏልና ነው

❉ አንድም ንስር ወደ ሰማይ መጥቆ ይበራል ወደ ምድርም ሲያይ ቅንጣት ታክል ሥጋ አታመልጠውም
ዮሐንስም አካል ከህልውና ተገልጦለት በንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ልቦና ተሰጥቶት
የቃልን ቀዳሚዊነትና ሥጋ መሆኑ ጽፏልና

2 ከአራቱ አፍላጋት በኤፍራጥሰ / በፈለገ ዘይት ይመስላል

❉ ዘይት/ወይራ ጽኑ ነው
ዮሐንስም ስለ ዓለም መከራና ከመከራውም ለመውጣት ብርቱ ጽናት
እንደሚያስፈልግ በመጻፉና ጽኑ እያለ በማስተማሩ /ዮሐ 16÷33/

❉ ዘይት በሩህ ነው

ወንጌላዊ ዮሐንስም በትምህርቱ የሰዎችን ልቡና ብሩህ ያደረገዋልና ነው

❉ አንድም ዘይት የሽቶ ዓይነቶችን ሰብስቦ አንድ ያደርጋል

ዮሐንስ የወንድሞቹን የወንጌላዊያንን ምሥጢር ጠቅልሎ በመጻፍ እንድ አድርጓቸዋልና ነው፡፡

3 ከአራቱ ባሕርያት ሥጋ በእሳት ይመሰላል

❉ እሳታዊ የሆነውን ነገረ መለኮትን አብዝቶ ጽፏልና ነው

4 ከ12ቱ እንቁዎች በአንዷ በመኀለቅ / መረግድ / ይመስላል፡፡
መኀለቅ ጠርዙ ሹል ስለታም ቀይ መልክ ያሉት ነው፡፡ /ራዕ. 21÷19 ትርጓሜ/

❉ ስለታም መሆኑ ሰማእታት በዚህ ዓለም መከራን ስለመቀበላቸው አብዝቶ ስለተነገረ ነው

❉ አንድም ሹል መሆኑ…ሹል በሆነ ነገር ድፍን የሆነውን ከፍተው እንደሚያወጡት ሁሉ
ለሃይማኖት ለምሥጢር ለዕውቀትና ለመጽሐፍ ድፍን የሆነ ልቡና ያላቸው መናፍቃንን
ድል የምነሳበት ሃይል ቃል አለውና ነው፡፡

❉ ቀይ እንደመሆኗ ለቤዛ-ዓለም እርሱ መድኀኔዓለም ደሙን እንዳፈሰሰ ጽፏልና ነው

5 ከአራቱ ወቅቶች መካከል በበጋ ይመስላል

❉ ይህ ወቅት መሬትዋ እሳት ላይ እንደተጣደ ብረት ምጣድ የምታቃጥልበት ነው
መሬቱ ደረቅ እንደሆነ ሁሉ ዮሐንስም ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር መናፍቃን ሊያጣምሙት የማይችሉትን
ደረቅ ቃል ነገረ መለኮትን አብዝቶ ጽፏልና ነው፡፡

6 ከአራቱ የያዕቆብ ሚስቶች በራሔል ይመስላል

❉ ያዕቆብ ከአራቱ ሚስቶቹ አብልጦ ይወዳት የነበረው ራሔልን ነው እንዲሁም ጌታ ከሌሎቹ ከደቀመዛሙርቱ ይልቅ ዮሐንስን ይወደው ነበርና ነው /የጌታ ወዳጅ ይለዋልን በመጽሐፍ/

❉ አንድም ራሔል በመጨረሻ ለያቆብ ልጁን እንደወለደችለት ሁሉ ዮሐንስም ወንጌሉን ከወንድሞቹ ኋላ /መጨረሻ/ ጽፏልና ነው
- ያዕቆብ …………….. የጌታ
- ልያና ራሔል ……….. የሐዋርያት ምሳሌ ናቸው፡፡
- ባለና ዘለፋ………….. የአርድእት

አበው ይናገሩ (ግጥም)

አበው ይናገሩ
"""""""""""ዘርዓቡሩክ ገ/ሕይወት(ምንጭ፡- መለከት 1ኛ ዓመት ቁጥር 6)


እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ
ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ፡፡

ነብያት በመጋዝ የተሰነጠቁት
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት
ምሥጢሩ ምን ነበር? አበው ይናገሩት፡፡

ይናገር ዝቋላ ግሸን ላሊበላ
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ፡፡
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡
ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት፡፡

ጐበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና፡፡
እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡
የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው?

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
የሃይማኖት ጀግና የትነው የማገኘው?
ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሐ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ፡፡

የት ነው የማገኘው ለሃይማኖቱ ሟች
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች፡፡
የወገን መመኪያ የከሀዲ መቅሰፍት
ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሣ ቀስቅሱት፡፡
እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ጀግና አማረው
በእምነቱ የፀና የትነው የማገኘው?
ብቅ ይበል እንየው እሱ ማነው ጀግና?

በጐችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ
የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?
የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?
ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር
ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን
ትንታግ ምላስም ጭንግፍግፉን
ልሳነ ጤዛ መናፍቅን
ወልደ አርዮስ ዲቃላውን፡፡
በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ
ጀግና ማነው ዝቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት
እስኪ ጎርጎርዮሰ ይምጣና ጠይቁት
ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ
ምሥጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ፡፡

የክርስቶስ ባርያ የአጋንንት መቅሰፍት
ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት
ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት
የጸሎት ገበሬ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ይነሣ ቀስቅሱት
ይነሣ ጊዮርጊስ ይመስክር ምሥጢር
የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ
ዲያብሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ፡፡
ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ
መር ብለው የወጡት ከሥጋ ገበያ
ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡

ገዳማዊ ህይወት

==> በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ገዳም አቡነ አረጋዊ የገደሙት ደብረ ዳሞ (ዙር አባ) ነው። በዚህ ገዳም አባታችን አቡነ አረጋዊ ለሠራዊቱ የሚሆን ውኃ እንዲፈልቅ በሚጸልዩበት ጊዜ 40 ምንጭ ፈልቋል።

==> በዓለም የመጀመሪያው ባህታዊ አባ ጳውሊ ሲሆን በዓለም የመጀመሪያውን ገዳም የገደመው ደግሞ አባ እንጦንስ ነው።

==> አባ ጳውሊ ከወንድሙ ጋር የአባታቸውን ንብረት በሚካፈሉበት ጊዜ ተጣሉ። በመንገድ ላይ ሲሄዱም ሰዎች አንድ የሬሳ ሳጥን ይዘው ሲጓዙ አዩ፤ አባ ጳውሊም የእኔም መጨረሻ ይኸው ነው! ወንድሜ ሆይ ከአንተ ጋር አልጣላም ብሎ ከኋላው ቀስ እያለ ተጓዘ፤ በመጨረሻም መንገዱን ቀይሶ ወደ በረሃ በመግባት በዓለም የመጀመሪያው ባህታዊ ሆኗል!

==> አባ እንጦንስም በቤተክርስቲያን ወንጌል ሲነበብ ሰማ፦ ፍጹም መሆን ብትፈልግ ያለህን ንብረት ሽጥና ተከተለኝ ማቴ [19: 22] የሚለውን ቃል ሰምቶ ያለውን ንብረት ሽጦ በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን ገዳም በግብጽ ምድር መሰረተ!

==> እንደነ አብርሐም መርዓዊ ከጫጉላ ቤታቸው ወተው ገዳማዊ ህይወትን የኖሩ ታላላቅ አባቶች አሉ።

==> ገዳማዊ ህይወትን ለአባቶችችን ያስተማሩትም መድኃኒተ ዓለም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ነቢዩ ኤልያስና መጥምቁ ዮሐንስ ናቸው።

አራት ሚስቶች

አራት ሚስቶች ያሉት አንድ ሰው ነበር።

አራተኛዋን ሚስቱን ከሁሉም አስበልጦ ይወድዳት፥ ይንከባከባትም ነበር።

ሶስተኛዋን ሚስቱንም ይወድዳት፥ ለጓደኞቹም ያሳያት ነበር። ነገር ግን “እኔን ጥላኝ፡ ከሌላ ወንድ ጋር ትኮበልላለች” ብሎ ሁሌም ይሰጋ ነበር።

ሁለተኛዋን ሚስቱንም ይወድዳት፡ ችግር በገጠመውም ግዜ ሁሉ ያዋያት ነበር፤ እሷም ሰለቸኝ፡ ደከመኝ ሳትል ዘወትር ትረዳው ነበር።

የመጀመሪያዋን ሚስቱን ግን ጭራሽ አይወድዳትም ፤ እርሷ ግን በተቃራኒው ከልብ ታፈቅረዋለች።

ከእለታት አንድ ቀን፡ ሰውዬአችን በጠና ታመመ፤ በህይወት ብዙም እንደማይቆይ ተረዳ።

“አራት ሚስቶች አሉኝ፤ ከሞትኩ በኋላ ብቸኝነት እንዳያጠቃኝ አንዷን ይዤ እሄዳለሁ።” ብሎም ወሰነ።

በዚህም መሰረት አራተኛውን ሚስቱን አብራው እንድትሞትና ከብቸኝነቱ እንድታስጥለው ጠየቃት።

“በጭራሽ አይሆንም!” ብቻ ብላ ሌላ ቃል ሳትተነፍስ ጥላው ሄደች።

ሶስተኛ ሚስቱን ተመሳሳይ ጥያቄ ሲጠይቃት

“እዚህ ህይወት ተመችቶኛል፤ ከሞትክ በኋላ ሌላ ባል አግብቼ እኖራለሁ” ብላ ተቃወመች።

ፊቱን ወደ ሁለተኛዋ ሚስቱ ቢያዞር

“አዝናለሁ! አሁን ልረዳህ አልችልም፤ ቢበዛ እስከ መቃብርህ ብከተልህ ነው።” ብላ አሳፈረችው።

ይህንን ተደጋጋሚ እንቢታ ሲሰማ፡ ልቡ በሀዘን ቀዘቀዘች።

ነገር ግን፡ ከጸጥታውና ከሀዘኑ መሀል፡ አንድ ድምጽ እንዲህ አለው፦

“እኔ አብሬህ እሄዳለሁ፤ የትም ብትሄድ እከተልሀለሁ።”

ሰውየው ቀና ቢል፡ ታማኝ ወዳጁን፡ የመጀመሪያ ሚስቱን ተመለከተ።

በቂ ምግብ ያላገኘች ሰው ትመስል በጣም ከስታናና ገርጥታ ነበር።

ድምጹ በከባድ ሀዘን እየተሰባበረ

“በጤና እያለሁ፡ የበለጠ ልንከባከብሽ ይገባኝ ነበር!” አላት።

እንደ እውነቱ ከሆነ፡ ሁላችንም አራት ሚስቶች/ባሎች አሉን።

1. አራተኛ ሚስት/ባል ሰውነታችን ነው።

ምንም ያህል ብንንከባከበው፡ ስንሞት አይከተለንም።

2. ሶስተኛ ሚስት/ባል ሀብትና ንብረታችን ነው።

ስንሞት ለሌሎች ይተላለፋል።

3. ሁለተኛ ሚስት/ባል ዘመድ ወዳጆቻችን ናቸው።

በህይወት እያለን ምንም ያህል ቅርቦቻችን ቢሆኑም፡ ከመቃብር ባሻገር አይከተሉንም።

4. የመጀመሪያ ሚስት/ባል ነፍሳችን ናት።

በምድር ላይ ቆይታችን ሀብትን እና ዝናን ስናሳድድ ችላ እንላታለን። በሄድንበት ቦታ ሁሉ አብራን የምትሄደው ግን እርሷው ብቻ ናት።

ስለዚህ ንስሀ እንግባ
ስለዚህ ንስሀ እንግባ
ስለዚህ ንስሀ እንግባ

"ሥርዓተ ቅዳሴ"

"ሥርዓተ ቅዳሴ"

በቅዳሴ ጊዜ ስለሚደረጉና ሰለማይደረጉ
ነገሮች ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
እንደሚከተለው ያዝዛል፦

1:በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን
የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ
ይጹም ይስገድ፣ የሳቀው ሕዝባዊ ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ
ይላል። ምነው ፍርድ አበላለጠ ካህኑን ተቀብሎ ወጥቶ ይቀጣ አለ፤ ሕዝባዊውን ሳይቀበል ወጥቶ ይሂድ አለ ቢሉ ካህኑ የሚቆመው ከውስጥ ነው ሲስቅ የሚያየው የለም። ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ቄስ እገሌ አባ እገሌ በመሥዋዕቱ ምን አይተውበታል ብለው መሥዋዕቱን ሳይቀር ይጠራጠሩታል፤ ስለዚህ ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤

2:በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤

3:በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።

4:በቤተ ክርስቲያንና በቅዳሴ ጊዜ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ ነገር የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት የጸሎት ቦታ ናትና::

5: ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣አይፈቀድም፣ በጣም ጭንቅ ምክንያት ወይም በሕመም ምክንያት ከሆን ግን ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ ሊወጣ ይችላል።

6:በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁን ነጭ ልብስ ደስ እንዲያሰኝ በሥጋ ወደሙ የተገኘ ክብርም ደስ ያሰኛልና፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ባህርየ መለኮቱን በገለጸ ጊዜ ልብሱ እንደበረድ ነጭ ሆኗል። መላእክትም ወርኃ ሰላም ወርኃ ፍስሐ ነው ሲሉ የልደት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።

7:አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት ፫-፭/ ።

8:በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዖውን የማያውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና ሆኖ ሕሊናው ወደ ዓለማዊ እንዳይወስደው መቆጣጠር አለበት።

9:ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ካህኑ ለሕዝቡ ተርጉሞ ይንገራቸው ያስተምራቸው እጁንም በሚታጠብበት ጊዜ የተጣላችሁ ሳትታረቁ፣ የሰው ገንዘብ የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ ሥጋ ወደሙን ብትቀበሉ ሥጋው እሳት ሆኖ
ይፈጃችኋል ደሙ ባህር ሆኖ ያሰጥማችኋል። ነገር ግን የወሰዳችሁትን የሰው ገንዘብ መልሳችሁ፣ ከተጣላችሁት ታርቃችሁ ኃጢአት ብትሰሩ ንስሐ ገብታችሁ ብትቀበሉት ግን መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ይሆናችኋል።
በረከተ ሥጋውን በረከተ ነፍሱን ያድላችኋል ብሎ ይንገራቸው ያስተምራቸው ይላል።

10:በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

11:በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያት ይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

12:ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው።ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልም “የጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለ” ይበል፣ ተሳላሚው ቄስም “መንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህ” ይበል። ለዲያቆናትም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣ ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህ” እያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህ” እያለ ይባርካቸው። ለሴቶችም “ልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽ” ብሎ በእጁ ይባርክ።

ሻካራ እጆች

ሻካራ እጆች
ዳንኤል ክብረት

የአንድ ኩባንያ ባለቤት ለደርጅቱ ብቁ የሆነ ሥራ አስኪያጅ ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣ፡፡

ላወጣው ማስታወቂያ ባቀረቡት ማስረጃ ተወዳድረው ካለፉት ሦስት ሰዎች መካከል በዕድሜ

ትንሽ የሆነውን ለቃለ መጠይቅ ጠራው፡፡

ወጣቱ በተጠራበት ቀን አለባበሱን አሳምሮ መንፈሱንም አንቅቶ ጠበቀ፡፡ የኩባንያው ባለቤት የወጣቱን የትምህርት እና የሥራ ሁኔታ የሚገልጠውን መረጃ አገላብጦ አየው፡፡ የተማረው በሀገሪቱ ውስጥ አንቱ በሚባሉ ት/ቤቶች ነው፡፡

የመጀመርያ እና ሁለተኛ ዲግሪውን የሠራው እጅግ በጣም ሀብታሞች በሚማሩባቸው ኮሌጆች ውስጥ ነው፡፡ ያገኛቸው ውጤቶች ምርጥ ከሚባሉት ውጤቶች ውስጥ ናቸው፡፡ በየደረጃው ከነበሩ መምህራን እና የትምህርት ባለሞያዎች ሽልማቶችን እና ማበረታቻዎችን አግኝቷል፡፡

የኩባንያው ባለቤት «ይህንን ሁሉ የትምህርት ክፍያ ይከፍልልህ የነበረው አባትህ ነው)»
ሲል ጠየቀው፡፡ ልጁም «አይደለም፤ አባቴን በልጅነቴ ነው ያጣሁት» ሲል መለሰለት፡፡

«ኦ ይቅርታ፤ ታድያ ስኮላርሺፕ አግኝተህ ነበር?» አለው፡፡

«እስካሁን በትምህርት ጉዞዬ ስኮላርሺፕ የሚባል አላጋጠመኝም» ብሎ ፈገግ አለ፡፡

«መቼም ከዘመዶችህ አንዱ የተሻለ ገቢ ያለው ሰው መሆን አለበት?» አለና የኩባንያው ባለቤትም ፈገግታውን በፈገግታ መለሰለት፡፡

«እኔ ሀብታም ዘመድ የለኝም፤ ኧረ እንዲያውም ዘመድ ራሱ የለኝም» አለው ወጣቱ፡፡

የኩባንያው ባለቤት እየተገረመ «ታድያ ይህንን በመሰሉ ት/ቤቶች ገብቶ ለመማር እኮ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፤ ማን እየከፈለልህ ነበር የምትማረው?» ሲል በአግራሞት ጠየቀው፡፡

«የምትከፍልልኝ እናቴ ነበረች» አለና ወጣቱ በኩራት መለሰ፡፡

«እናትህ ምን ዓይነት ሥራ ነው የምትሠራው?» አለው ባለቤቱ፡፡

«እናቴ የሰዎችን ልብስ እየሰበሰበች የምታጥብ ሴት ናት» አለው ወጣቱ፡፡

«ልብስ እያጠበች ነው አንተን ይህንን በመሳሰሉ ት/ቤቶች ያስተማረችህ?»

«አዎ»

«አንድ ጊዜ እጅህን ለማዬት እችላለሁ» አለው የኩባንያው ባለቤት፡፡ ወጣቱ እጁን ወደ ባለቤቱ ላከው፡፡ እጁ ከኬክ የለሰለሰ ነበረ፡፡

«ለመሆኑ እናትህን በልብስ አጠባው ረድተሃት ታውቃለህ?»

«አላውቅም»

«ለምን?»

«እናቴ እኔ ምንም ሥራ እንድሠራ አትፈልግም፤ እንድማር፣ እንዳጠና እና እንዳልፍ ብቻ ነው የምትፈልገው፤ ስለዚህ ሥራ ሠርቼ አላውቅም»

«በጣም ጥሩ» አለ የኩባንያው ባለቤት «ቃለ መጠይቁን ነገ እንቀጥላለን፤ አሁን ወደ ቤትህ ሂድና አንድ ነገር አድርግ» አለው፡፡

ወጣቱ እየገረመው «ምን?» አለ፡፡

«የእናትህን እጆች እጠብ፤ ከዚያ የሆነውን ነገ ትነግረኛለህ»

በቃለ መጠይቁ የተሻለ ነገር አድርጌያለሁ ብሎ እያሰበ በደስታ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
ቤቱ ገብቶ እናቱን እጇን ለማጠብ ጠየቃት፡፡ አዲስ ነገር ሆነባትና ጠየቀችው፡፡ እርሱም ዛሬ ያጋጠመውን ነገር አጫወታት፡፡

ውኃ እና ሳሙና አቀረበና የእናቱን እጆች ማጠብ ጀመረ፡፡ የተኮራመቱ፤ የተሰነጣጠቁ፤ የቆሳሰሉ፤ የተጠባበሱ፤ እጆች፡፡ የእርሱን እና የእናቱን እጆች እያስተያየ ማልቀስ ጀመረ፡፡

ከሚያጥብበት ውኃ ይልቅ እርሱ የሚያነባው ዕንባ በለጠ፡፡ እነዚህ እጆች እንዲህ የሆኑት እርሱን ለማስተማር መሆኑን አሰበ፡፡

እነዚህ ጠባሶች የእርሱ ጠባሶች ናቸው፡፡

እነዚህ ቁስሎች የእርሱ ቁስሎች ናቸው፤

እነዚህ እጆች ናቸው ለእርሱ የትምህርት ውጤት መሠረቶቹ፣

እነዚህ እጆች ናቸው እርሱን ለአካዳሚያዊ ውጤት ያበቁት፤

እነዚህ እጆች ናቸው ዛሬ ለቆመበት ታላቅ ደረጃ ያበቁት፡፡

የእናቱን እጆች አጥቦ ሲጨረስ የቀሩትን ልብሶች ሁሉ ከእናቱ ጋር አጠበ፡፡

በዚያች ሌሊት ያ ልጅ ከእናቱ ጋር ለረዥም ሰዓት ሲያወሩ አደሩ፡፡

ነግራው የማታውቀውን ታሪክ ነገረችው፤ ሰምቶት የማያውቀውን ታሪክም ሰማ፡፡

በማግስቱ ወጣቱ ወደ ኩባንያው ባለቤት ዘንድ ሄደ፡፡ የኩባንያው ባለቤት የወጣቱን ዓይኖች ሲያይ የዕንባዎቹን ፈለግ ተመለከተ፡፡ እናም «ትናንት ያደረግከውን እና ያጋጠመህን ልትነግረን ትችላለህ)» ሲል ጠየቀው፡፡

«የእናቴን እጆች አጠብኳቸው፡፡ የእናቴ እጆች እንደዚህ መሆናቸውን አላውቅም ነበር፡፡ ብዙ ነገር ነገረችኝ፤ ልብሶቹንም አብሬያት አጠብኩ» አለው፡፡

«ታድያ ምን ተማርክ?» አለው የኩባንያው ባለቤት፡፡

«ሦስት ነገሮችን ተምሬያለሁ» አለ ወጣቱ፡፡

«መጀመርያ ነገር አድናቆት እና ምስጋናን ተምሬያለሁ፡፡ እናቴ ባትኖር ለእኔም ያንን ሁሉ መከራ ባትቀበል ኖሮ ዛሬ የደረስኩበት ልደርስ አልችልም ነበር፡፡ ስለዚህ እናቴን ምንጊዜም ላመሰግን፤ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ቀድሜ ስሟን ልጠራ፤ ስለ ራሴ ከመናገሬ በፊት ስለ እርሷ ልናገር እንደሚገባ ተረድቻለሁ፡፡

ሁለተኛ ደግሞ እናቴ ያለፈችበትን እውነተኛው ነገር መረዳት የቻልኩት አብሬያት ሆኜ ሥራዋን ስጋራት ነው፡፡ በሱታፌ ካልሆነ በቀር በነቢብ እና በትምህርት ብቻ የአንድን ነገር ርግጠኛ ጠባይ እና ሁኔታ መረዳት አይቻልም፡፡

ሦስተኛ ደግሞ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ መኖር ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊ ትሥሥርም ወሳኝ መሆኑን አይቻለሁ፡፡» አለው

የኩባንያውም ባለቤት «የምፈልገው ሥራ አስኪያጅ አሁን ተገኘ፡፡ ለእርሱ ሕይወት ሌሎች የከፈሉትን ሰማዕትነት የሚረዳ፤ አብሮ በመሥራት ችግሮችን መቅመስን እና መፍታትን የተማረ፤ የሥራ ግቡ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ያልሆነ ሰው አሁን ተገኘ» አለና ቀጠረው ይባላል፡፡

ከኛ ሕይወት ጀርባ ስንት ሰዎች አሉ?

ለመሆኑ ዋጋ እንሰጣቸዋለን?

እናመሰግናቸዋለን?

ስማቸውን እንጠራለን?

የቀመሱትን መከራ እናውቅላቸዋለን) ችግራቸውን እንሳተፍላቸዋለን?

ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር፣ ፓትርያርክ፣ ጳጳስ፣ ሼህ፣ ዑላማ፣ ምሁር፣ ሳይንቲስት፣ ነጋዴ፣ አትሌት፣ አርቲስት፣ ሰባኪ፣ ፓስተር፣ ሐኪም፣ ፖለቲከኛ፣ ገበሬ፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ወዘተ፣ ወዘተ ስንሆን ብቻችንን ነበርን?

እኛ እዚህ እንድንደርስ ስንቶች ሰማዕትነት ከፈሉ? የስንት ሰዎች ወዝ ፈሰሰ፣ ላብ ተንቆረቆረ፣ ገንዘብ ተከሰከሰ፣ ጨጓራ ተላጠ፣ አንጀት ተቃጠለ?

አምፖሎቹ ዝም ብለው አልበሩም፡፡ አምፖሎቹ እንዲበሩ ያደረገው ጀነሬተሩ ነው፡፡ ጀነሬተሩ ግን አይታይም፡፡ የሚታዩት አምፖሎቹ ናቸው፡፡ ሰዎችም የሚያውቋቸው አምፖሎቹን ነው፡፡ አብዛኛው ሰው አምፖሎቹን ለማሳመር እና በአምፖሎቹ ውበትም ቤቱን ለማሳመር ይጥራል እንጂ ስለ ጀነሬተሩ አይጨነቅም፡፡ ወሳኙ ግን እርሱ ነው፡፡

ጀነሬተሮቻችን እነማን ናቸው? እነዚህ ጀነሬተሮች ናቸው በሃይማኖት ቅዱሳን፣ በሀገር ቀደምት አባቶች፣ በዕውቀት ፋና ወጊዎች፣ በነጻነት አርበኞች፣ እየተባሉ የሚጠሩት፡፡

ያለ እነዚህ እምነት፣ ሀገር፣ ነጻነት፣ ክብር፣ ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ዕድገት፣ ብልጽግና የሚባሉ ቃላት ውኃ አይቋጥሩም ነበር፡፡

የዚያ ልጅ ችግሩ መማሩ አልነበረም፣ የተሻለ ውጤት ማምጣቱም አይደለም፤ የተማረበትን እና የተሻለ ውጤት ያመጣበትን ምክንያት መርሳቱ ነው፡፡

መማሩን ያውቃል፤

እንዴት ሊማር እንደቻለ ግን አያውቅም፡፡

ለዚያ ውጤት ያበቃው ማጥናቱ፣ ተግቶ መሥራቱ እና የአእምሮ ብቃቱ ብቻ መስሎ

ሊታየውም ይችላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ መሠረታቸው እናቱ ናት፡፡

እናቱ መሥዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ ባትሆን ኖሮ እነዚህ ሁሉ ገደል ይገቡ ነበር፡፡ ስንት አእምሮ ያላቸው ሰዎች ደጋፊ በማጣት ጎዳና ላይ ቀርተዋልኮ፤ ስንት ተግተው ማጥናት የሚችሉ ጎበዝ ተማሪዎች አጋዥ በማጣት አቋርጠዋልኮ፡፡

ለቀደምቶቻችን ዋጋ ካልሰጠን ለኛ ዋጋ የሚሰጥ ትውልድ አይፈጠርም፡፡ መነሻችንን ካላወቅን በመድረሻችን አናመሰግንም፡፡

ችግሮችን ካልቀመስን አማራሪዎች እና ጨካኞች እንሆናለን፡፡ ለእኛ ሕይወት ሌሎች ለከፈሉት ዋጋ ካልሰጠን እኛም ለሌሎች ሕይወት ምንም አንከፍልም፡፡ እኛ እንድናድግ ያደረጉትን ከዘነጋን ሌሎች እንዲያድጉ አናደርግም፤ ለኛ ሲባል ቀደምቶቻችን የቀመሱትን መከራ ካላሰብን እንዴትስ ለሌሎች ብለን መከራ እኛ እንቀምሳለን?

ሕይወት እንደ አውሮፓ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ አይደለችም፡፡

ይዞ ማለፍ እንጂ፡፡

ምኒሊክን እየናቅን አዲስ አበባ ላይ መኖር፤ ዐፄ ፋሲልን ረስተን ጎንደር ግንብን ማስጎብኘት፤ ንግሥተ ሳባን ዘንግተን አኩስም ጽዮንን ማንገሥ እንዴት ይቻላል? ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ያለ አበበ ቢቂላ እንዴት ማሰብ ይቻላል?

እናቱም ይህንን ሁሉ ብታደርግም አንድ የሚቀራት ነገር ግን ነበር፡፡ አልነገረችውም፡፡ የስኬቱን ምሥጢር አልነገረችውም፡፡

ወላጆች ለልጆቻቸው መንገር አለባቸው፡፡

የሚገዛው ኬክ፣

የሚገመጠው ዳቦ፣

የሚጫወቱበት መጫወቻ፣

የሚዝናኑበት ገንዘብ፣

የሚማሩበት ምርጥ ት/ቤት ክፍያ፣

የሚለብሱት ውድ ልብስ፣

የሚተኙበት ምቹ አልጋ እንዲሁ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የመጣ አይደለም፡፡

ደም ተተፍቶበት የተገኘ ነው፡፡

ይህንን ማወቅ አለባቸው፡፡

ቢያንስ ቢያንስ ሌላ ማድረግ ቢያቅታቸው የወላጆቻቸውን ሻካራ እጆች ማጠብ አለባቸው፡፡

ስሜቱን ስሜታቸው፣ ጉዳቱን ጉዳታቸው ማድረግ አለባቸው፡፡

ያለበለዚያ ወላጆቻቸውን አያመሰግኑም፣ አያደንቁም፣ አያከብሩም፡፡

የበሉበትን ወጭት መሥበር፣

ያጎረሰን እጅ መንከስ፣

ያሳደገን ትከሻ መርገጥ፣

ያሳደገው ሀገርም፣ ሕዝብም ተቋምም፣ ማኅበርም የለም፡፡

እንድንኖር ሲባል የሞቱ፤ እንድንድን ሲባል የቆሰሉ፤

እንድንማር ሲባል ያልተማሩ፤

እንድንጠግብ ሲባል የተራቡ፤

እንድንለብስ ሲባል የታረዙ፤

እንድንበለጽግ ሲባል የደኸዩ አሉ፡፡

እነዚህ አካላት ከፍ ያለ ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ስማቸው ከስማችን፤

ክብራቸው ከክብራችን መቅደም አለበት፡፡

ሻካራ እጆቻቸው የስኬታችን መሠረቶች ናቸው፡፡

እናጥባቸዋለን፤ እንስማቸዋለን፣ እንኮራባቸዋለንም፡፡

እናጥባቸዋለን፤ እንስማቸዋለን፣ እንኮራባቸዋለንም፡፡

እናጥባቸዋለን፤ እንስማቸዋለን፣ እንኮራባቸዋለንም፡፡

ያለ እኛ ኖረዋል፡፡ ያለ እነርሱ ግን አንኖርም ነበር፡፡

እነርሱ በእኛ ያበቃሉ፤ እኛ ግን በእነርሱ እንጀምራለን፡፡

ሻካራ እጆች ሆይ ከፍ ከፍ በሉ፤ ክብር እና ምስጋና ለእናንተ ይሁን፡፡

እኛ በእናንተ እንኮራለን፤ እናንተም በእኛ ትጠራላችሁ፡፡

ያለ ሻካራ እጆች ለስላሳ እጆች ከየት ይገኙ ነበር፡፡

ኦ ሸካራ እጆች ሆይ፤ ለሸካራነታችሁ ሰላም እላለሁ እኔን አለስልሶኛልና
ኦ ጠባሳ እጆች ሆይ፤ ለጠባሳችሁ ሰላም እላለሁ፤ እኔን አስውቦኛልና
ኦ የቆሰሉ እጆች ሆይ፤ ለቁስላችሁ ሰላም እላለሁ፤ እኔን አድኖኛልና
ኦ ጎርባጣ እጆች ሆይ፤ ለጎርባጣነታችሁ ሰላም እላለሁ፤ እኔን አክብሮኛልና፡፡

የቅዱስ ያሬድ ታሪክ

የቅዱስ ያሬድ ታሪክ

ቅዱስ ያሬድ በ505 ዓ/ም በአክሱም ተወለደ። አባቱ አብዩድ ወይም ይስሐቅ እናቱም ክርስቲና ወይም ታውክልያ ይባሉ ነበር። የነርሱም ሀገራቸውና ርስታቸው አክሱም ነበር። ቅዱስ ያሬድ በተወለደ በ7 ዓመቱ አባቱ ስለሞተ እናቱ ክርስቲና የአክሱም ገበዝ ለነበረው ለአጎቱ ለጌዲዎን እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው አደራ ብላ ሰጠችው። ከጌዴዎንም ቤት 25 ዓመት እስኪሆነው እየተማረ አደገ። ከዚያም መፃህፍትን ማለት ብሉይንና አዲስን ተማረ። ከዚህም በኋላ መምህሩ (አጎቱ) ጌዴዎን ሲሞት እርሱ ተተክቶ የመጽሐፍ መምህር ሆነ። በዚህም ጊዜ በዲቁና ሚስት አግብቶ ልጆችን ወለደ። ቀጥሎም ቄስ ሆነ።

በእርሱም ዘመን 9ኙ ቅዱሳን ከውጭ አገር በችግር ምክንያት ተሰደው ስለመጡ፤ ይህም ማለት በቁስጥንጥንያ መንግሥት ዮስጥንያኖስ ዩስቲኒያኖስ በነገሠበት ከ527 ዓ/ም እስ ከ 565 ዓ/ም ድረስ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድ ባሕርይና በሁለት ባሕርይ ወገኖች ውስጥ ብዙ ሁከትና ፍጅት ስለነበረ ከዚያ በመሸሽ የመጡ ካህናትና መነኮሳት ስለነበሩ ከእነርሱም አንዱ በአክሱም ከተማ አጠገብ የነበረው አባ ጰንጠሊዎን ስለነበር፤ ቅዱስ ያሬድ እየተመላለሰ የውጭውን አገር ቤት ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቀው ነበር ይባላል።

ከዚያም በኋላ ቅዱስ ያሬድ የውጭውን አገር ቤት ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ለመጎብኘት ሁለት ጊዜ ተመላልሼ የሮምን ቤተ ክርስቲያን፤ 2ኛይቱን ሮም የተባለችውን የምሥራቅና የቁስጥንጥንያን ቤተ ክርስቲያን ጎበኘሁ’ ሲል በመዝሙሩ እርሱ ራሱ ገልፆልናል። (ወሪድዬ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርኢክዋ አእመርክዋ አፍቀርክዋ ከመ እኅትየ ሠናይ ሐለይኩ፤ እምድኅረ ጉንዱይ ዓመታት ወእምዝ እምድኅረ ኅዳጥ መዋዕል ካዕበ ርኢክዋ ወትትሐጸብ በፈለገ ጤግሮስ) እንደዚህ እያለ የውጭውን አገር ቤተ ክርስቲያን ሲያመሰግን ይገኛል።

ከሱ በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደንበኛ የሆነ ቅኔና ዜማ ትምህርት ስለሌለ ደንበኛ የሆነ ቅኔና ዜማ ለማስገኘት ተዘጋጀ። የድርጅቱም መጀመሪያ ይህ ነበር። ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ፤ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ብሎ ከነበሩት ከብሉይና ከሐዲስ ሊቃውንት አንዱ እርሱ ስለ ነበርና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ አሳብ ስለነበረው ከብሉይና ከሐዲስ፣ ከሊቃውንት መጻሕፍትም ከነአትናቴዎስ ከነቄርሎስ ከነዮሐንስ አፈወርቅ መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የተስማሙትን ቃላት እየመረጠና እያቀና በአራቱ ክፍለ ዘመን፣ በመፀውና በሐጋይ በጸደይና በክረምት እንዲነገር አድርጎ ወስኖ አዘጋጀ።

የመጽሐፉ (የድርሰቱ) ስም ድጓ ተባለ። ድጓ ማለትም በአክሱምና በአድዋ ቋንቋ (በትግርኛ) ደጉዓ ማለት መዝሙረ ኃዘን፥ የኃዘን ዜማ፥ ማለት ነው። – ሙሾ። የዜማውን ዓይነት በሦስት ክፍል ወስኖ ተናግሮታል። እነርሱም ግዕዝ፣ ዕዝል፣ ዓራራይ ይባላሉ። ግዕዝ ማለትም አንደኛ በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው፤ ዕዝል ማለትም ሁለተኛ ሆኖ ከግዕዙ ጋር ተደርቦ፣ ተጨምሮ (ታዝሎ) የሚነገር ማለት ነው። ዓራራይ ማለትም ሦስተኛ ተጨማሪ ሆኖ አራኅራኂ፣ ርኅራኄ/አሳዛኝ ልብን የሚመስጥና ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው። ይህን ድርሰቱን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540 ዓ/ም ሲሆን የመጨረሻ ልጁ አፄ ገብረ መስቀል መንግሥቱን ወረሰ።

አፄ ገብረ መስቀልና አባ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ሦስቱ በአንድነት እንደነበሩ ታሪከ ነገሥቱና ገድለ አረጋዊ ይገልጽልናል። አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞን ተራራ አቀማመጥ አይተው ደስ ስላላቸው፣ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ተራራ ላይ እንዲኖሩበትና እንዲጸልዩበት ፈቀደላቸው። እርሳቸውም ይህንን ተራራ ከተረከቡ በኋላ በተራራው ላይ የጸሎት ቤት ስለሌለ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልን አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው ለመኑት። ንጉሡም ቤተክርስቲያን ልሠራ የምችልበትን ሥፍራ መርጠው ያመልክቱኝ ብሎ ነገራቸው አቡነ አረጋዊም ተነሥተው ዞረው ቦታውን መርጠው አሳዩት።

ከዚህ በኋላ ንጉሡ በአዋጅና በትዕዛዝ ድንጋዩና እንጨቱ እየተሰበሰበ በከብትና በሠረገላ እየተጋዘ ተሰበሰበና ከታች ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ተሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በሁለት ዓመት አለቀ። ባለቀም ጊዜ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ተመልካቾችን አስደነቀ። ለዚሁም ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የሆኑ አልባሳት፣ የብርና የወርቅ የተደጎሱና የተከፈፉ መጻሕፍትን አበረከቱ። ከማኅበረ በኩር የመጣውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጽላት አግብተው አቡነ አረጋዊ ባርከውና ቀድሰው ንጉሡና ጳጳሱ ቆረቡ። ከዚያም አፄ ገብረ መስቀል በተራራው ላይና በግርጌ ላሉት ሠራዊት ግብር አብልተው ነዳያን ሁሉ ጠገቡ።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ሲያስተምር ሳለ በንጉሡ አፄ ገብረመስቀልና አቡነ አረጋዊ፥ ወደዚህ ተራራ መጥቶ ቤተክርስቲያኑን እንዲጎበኝና እንዲዘምር ተጠርቶ ሲመጣ ከተራራው ሥር ሲደርስ የአቡነ አረጋዊን ደቀመዛሙርት ማትያስና ዮሴፍ የሚባሉትን ከወንዝ ዳር ዓሣ ሲያጠምዱ አግኝቶ ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ (ይህ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው?) ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ደኅንነታቸውን ነገሩት። ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ከአቡነ አረጋዊ ጋር በመንፈሳዊ አምኃ በፍቅር ተገናኙ ወደ ቤተክርስቲያኑም ሄዶ 3 ጊዜ ሰግዶ ከተሳለመ በኋላ የሕንጻውን ማማር በአድናቆት ተመልክቶ ከፍ ባለ የዜማ ድምፅ እያጉረመረመ እንዲህ ሲል ዘመረ።

‘ይሄውፅዋ መላዕክት እንተ በሰማያት ይሄውፅዋ መላዕክት እስመ ማኅደረ መለኮት ፆድክዋ ፆድክዋ ፆድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፄሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥአል ወምስጋድ ወምሥትስራየ ኃጢአት ይዕቲ ቅድስት ደብተራ።’ የሚለውን መዝሙር ከዘመረ በኋላ ስምንት ቀን ያህል ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሰንብቶ ንጉሡ ወደ አለበት ወደ አኩሱም ተመልሶ ሲገባ አንቀጸ ብርሃን ተብሎ የተሰየመውን ድርሰትን ቅድስት ወብፅዕት ብሎ በዜማ ደረሰ። ከዚህ በኋላ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ ከቅዱስ ያሬድ ጋር አብረው ወደ ሌላ ጠቅላይ ግዛት ጉብኝት ሄዱ። ከዚያም በአንዱ ደሴት ላይ የቅዱስ ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቀመጡ። በዚያም ቦታ ቅዱስ ያሬድ ሁለት ዓመት አስተማረ። እርሱ እራሱ ጻፈው የሚባል ድጓ ምልክት የሌለው ዛሬ በዚሁ ደሴት በጣና ቂርቆስ ይገኛል።

ከዚህም ደሴት ከጣና ቂርቆስ ተነሥተው ንጉሡና አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድም ወደ ደጋው ወደ ጋይንት ወጡ። በዚያም አንድ ትልቅ ተራራ አግኝተው መውጫው ጠፍቶባቸው ሲጨነቁ አንድ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልዕክተኛ መጥቶ አቡነ አረጋዊን (ዙር አባ መንገለ ምሥራቅ) አባ መውጫውን በምሥራቅ በኩል ታገኘዋለህ ሲል አመለከታቸውና ሦስቱም ተያይዘው ወደ ተራራው ላይ ወጡ። በዚሁ ተራራ ላይ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠሩ። የተራራውም ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዙር አምባ ተብሎ ይጠራል።ቅዱስ ያሬድ በዚሁ ተራራ ላይ ሦስት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለውን መዝሙር አስተምሯል። ይህም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የዝማሬና የመዋሥዕት ምስክር ቦታ ሆኖ ይኖራል።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ አክሱም ተመልሶ ለሥጋ ወደሙ ጸሎት የሚያገለግሉትን 14ቱን ቅዳሴዎች በዜማ ተናገረ። ቅዳሴውን በዜማ የተናገረበት ቦታ መደባይታብር ይባላል። ይህም መደባይታብር የሚባለው ቦታ ለአክሱም ሰሜን ሆኖ ከአክሱም ግማሽ ቀን ያህል በእግር ያስኬዳል። ከዚያም ወደ ሰሜን ተራራዎች ወደ ጠለምት ሔዶ ምዕራፍ የተባለውን የዳዊትን መዝሙር ተናገረ። ከዚህ በኋላ ወደ ወገራና ወደ አገው እየዞረ ካስተማረ በኋላ ከሰሜን ተራራዎች ሥር ባሉት በአንዱ ገዳም ውስጥ በብሕትውና ከቆየ በኋላ በሰሜን ምሥራቅ ባለው ሸዋ ውስጥ በ571 ዓ/ም ግንቦት 11 ቀን አረፈና ተቀበረ።

ከዚህ በኋላ የእርሱ ደቀመዛሙርት ሳዊሮስና ሳንድሮስ በልዳዶስ የሚባሉት ከርሱ የተማሩትን የዜማ ባሕልና ሥርዓት በትግሬና በሰሜን አውራጃ እየተዘዋወሩ በየገዳማቱ ሁሉ ስለአስተማሩ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንቶ ይኖራል።

ምንጭ:“የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የዜማው ምልክቶች” ግንቦት 15/ 1959 በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የታተመ መጽሐፍ

ቅዱስ ያሬድ በ505 ዓ/ም በአክሱም ተወለደ። አባቱ አብዩድ ወይም ይስሐቅ እናቱም ክርስቲና ወይም ታውክልያ ይባሉ ነበር። የነርሱም ሀገራቸውና ርስታቸው አክሱም ነበር። ቅዱስ ያሬድ በተወለደ በ7 ዓመቱ አባቱ ስለሞተ እናቱ ክርስቲና የአክሱም ገበዝ ለነበረው ለአጎቱ ለጌዲዎን እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው አደራ ብላ ሰጠችው። ከጌዴዎንም ቤት 25 ዓመት እስኪሆነው እየተማረ አደገ። ከዚያም መፃህፍትን ማለት ብሉይንና አዲስን ተማረ። ከዚህም በኋላ መምህሩ (አጎቱ) ጌዴዎን ሲሞት እርሱ ተተክቶ የመጽሐፍ መምህር ሆነ። በዚህም ጊዜ በዲቁና ሚስት አግብቶ ልጆችን ወለደ። ቀጥሎም ቄስ ሆነ።

በእርሱም ዘመን 9ኙ ቅዱሳን ከውጭ አገር በችግር ምክንያት ተሰደው ስለመጡ፤ ይህም ማለት በቁስጥንጥንያ መንግሥት ዮስጥንያኖስ ዩስቲኒያኖስ በነገሠበት ከ527 ዓ/ም እስ ከ 565 ዓ/ም ድረስ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድ ባሕርይና በሁለት ባሕርይ ወገኖች ውስጥ ብዙ ሁከትና ፍጅት ስለነበረ ከዚያ በመሸሽ የመጡ ካህናትና መነኮሳት ስለነበሩ ከእነርሱም አንዱ በአክሱም ከተማ አጠገብ የነበረው አባ ጰንጠሊዎን ስለነበር፤ ቅዱስ ያሬድ እየተመላለሰ የውጭውን አገር ቤት ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቀው ነበር ይባላል።

ከዚያም በኋላ ቅዱስ ያሬድ የውጭውን አገር ቤት ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ለመጎብኘት ሁለት ጊዜ ተመላልሼ የሮምን ቤተ ክርስቲያን፤ 2ኛይቱን ሮም የተባለችውን የምሥራቅና የቁስጥንጥንያን ቤተ ክርስቲያን ጎበኘሁ’ ሲል በመዝሙሩ እርሱ ራሱ ገልፆልናል። (ወሪድዬ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርኢክዋ አእመርክዋ አፍቀርክዋ ከመ እኅትየ ሠናይ ሐለይኩ፤ እምድኅረ ጉንዱይ ዓመታት ወእምዝ እምድኅረ ኅዳጥ መዋዕል ካዕበ ርኢክዋ ወትትሐጸብ በፈለገ ጤግሮስ) እንደዚህ እያለ የውጭውን አገር ቤተ ክርስቲያን ሲያመሰግን ይገኛል።

ከሱ በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደንበኛ የሆነ ቅኔና ዜማ ትምህርት ስለሌለ ደንበኛ የሆነ ቅኔና ዜማ ለማስገኘት ተዘጋጀ። የድርጅቱም መጀመሪያ ይህ ነበር። ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ፤ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ብሎ ከነበሩት ከብሉይና ከሐዲስ ሊቃውንት አንዱ እርሱ ስለ ነበርና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ አሳብ ስለነበረው ከብሉይና ከሐዲስ፣ ከሊቃውንት መጻሕፍትም ከነአትናቴዎስ ከነቄርሎስ ከነዮሐንስ አፈወርቅ መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የተስማሙትን ቃላት እየመረጠና እያቀና በአራቱ ክፍለ ዘመን፣ በመፀውና በሐጋይ በጸደይና በክረምት እንዲነገር አድርጎ ወስኖ አዘጋጀ።

የመጽሐፉ (የድርሰቱ) ስም ድጓ ተባለ። ድጓ ማለትም በአክሱምና በአድዋ ቋንቋ (በትግርኛ) ደጉዓ ማለት መዝሙረ ኃዘን፥ የኃዘን ዜማ፥ ማለት ነው። – ሙሾ። የዜማውን ዓይነት በሦስት ክፍል ወስኖ ተናግሮታል። እነርሱም ግዕዝ፣ ዕዝል፣ ዓራራይ ይባላሉ። ግዕዝ ማለትም አንደኛ በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው፤ ዕዝል ማለትም ሁለተኛ ሆኖ ከግዕዙ ጋር ተደርቦ፣ ተጨምሮ (ታዝሎ) የሚነገር ማለት ነው። ዓራራይ ማለትም ሦስተኛ ተጨማሪ ሆኖ አራኅራኂ፣ ርኅራኄ/አሳዛኝ ልብን የሚመስጥና ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው። ይህን ድርሰቱን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540 ዓ/ም ሲሆን የመጨረሻ ልጁ አፄ ገብረ መስቀል መንግሥቱን ወረሰ።

አፄ ገብረ መስቀልና አባ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ሦስቱ በአንድነት እንደነበሩ ታሪከ ነገሥቱና ገድለ አረጋዊ ይገልጽልናል። አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞን ተራራ አቀማመጥ አይተው ደስ ስላላቸው፣ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ተራራ ላይ እንዲኖሩበትና እንዲጸልዩበት ፈቀደላቸው። እርሳቸውም ይህንን ተራራ ከተረከቡ በኋላ በተራራው ላይ የጸሎት ቤት ስለሌለ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልን አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው ለመኑት። ንጉሡም ቤተክርስቲያን ልሠራ የምችልበትን ሥፍራ መርጠው ያመልክቱኝ ብሎ ነገራቸው አቡነ አረጋዊም ተነሥተው ዞረው ቦታውን መርጠው አሳዩት።

ከዚህ በኋላ ንጉሡ በአዋጅና በትዕዛዝ ድንጋዩና እንጨቱ እየተሰበሰበ በከብትና በሠረገላ እየተጋዘ ተሰበሰበና ከታች ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ተሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በሁለት ዓመት አለቀ። ባለቀም ጊዜ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ተመልካቾችን አስደነቀ። ለዚሁም ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የሆኑ አልባሳት፣ የብርና የወርቅ የተደጎሱና የተከፈፉ መጻሕፍትን አበረከቱ። ከማኅበረ በኩር የመጣውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጽላት አግብተው አቡነ አረጋዊ ባርከውና ቀድሰው ንጉሡና ጳጳሱ ቆረቡ። ከዚያም አፄ ገብረ መስቀል በተራራው ላይና በግርጌ ላሉት ሠራዊት ግብር አብልተው ነዳያን ሁሉ ጠገቡ።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ሲያስተምር ሳለ በንጉሡ አፄ ገብረመስቀልና አቡነ አረጋዊ፥ ወደዚህ ተራራ መጥቶ ቤተክርስቲያኑን እንዲጎበኝና እንዲዘምር ተጠርቶ ሲመጣ ከተራራው ሥር ሲደርስ የአቡነ አረጋዊን ደቀመዛሙርት ማትያስና ዮሴፍ የሚባሉትን ከወንዝ ዳር ዓሣ ሲያጠምዱ አግኝቶ ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ (ይህ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው?) ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ደኅንነታቸውን ነገሩት። ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ከአቡነ አረጋዊ ጋር በመንፈሳዊ አምኃ በፍቅር ተገናኙ ወደ ቤተክርስቲያኑም ሄዶ 3 ጊዜ ሰግዶ ከተሳለመ በኋላ የሕንጻውን ማማር በአድናቆት ተመልክቶ ከፍ ባለ የዜማ ድምፅ እያጉረመረመ እንዲህ ሲል ዘመረ።

‘ይሄውፅዋ መላዕክት እንተ በሰማያት ይሄውፅዋ መላዕክት እስመ ማኅደረ መለኮት ፆድክዋ ፆድክዋ ፆድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፄሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥአል ወምስጋድ ወምሥትስራየ ኃጢአት ይዕቲ ቅድስት ደብተራ።’ የሚለውን መዝሙር ከዘመረ በኋላ ስምንት ቀን ያህል ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሰንብቶ ንጉሡ ወደ አለበት ወደ አኩሱም ተመልሶ ሲገባ አንቀጸ ብርሃን ተብሎ የተሰየመውን ድርሰትን ቅድስት ወብፅዕት ብሎ በዜማ ደረሰ። ከዚህ በኋላ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ ከቅዱስ ያሬድ ጋር አብረው ወደ ሌላ ጠቅላይ ግዛት ጉብኝት ሄዱ። ከዚያም በአንዱ ደሴት ላይ የቅዱስ ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቀመጡ። በዚያም ቦታ ቅዱስ ያሬድ ሁለት ዓመት አስተማረ። እርሱ እራሱ ጻፈው የሚባል ድጓ ምልክት የሌለው ዛሬ በዚሁ ደሴት በጣና ቂርቆስ ይገኛል።

ከዚህም ደሴት ከጣና ቂርቆስ ተነሥተው ንጉሡና አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድም ወደ ደጋው ወደ ጋይንት ወጡ። በዚያም አንድ ትልቅ ተራራ አግኝተው መውጫው ጠፍቶባቸው ሲጨነቁ አንድ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልዕክተኛ መጥቶ አቡነ አረጋዊን (ዙር አባ መንገለ ምሥራቅ) አባ መውጫውን በምሥራቅ በኩል ታገኘዋለህ ሲል አመለከታቸውና ሦስቱም ተያይዘው ወደ ተራራው ላይ ወጡ። በዚሁ ተራራ ላይ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠሩ። የተራራውም ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዙር አምባ ተብሎ ይጠራል።ቅዱስ ያሬድ በዚሁ ተራራ ላይ ሦስት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለውን መዝሙር አስተምሯል። ይህም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የዝማሬና የመዋሥዕት ምስክር ቦታ ሆኖ ይኖራል።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ አክሱም ተመልሶ ለሥጋ ወደሙ ጸሎት የሚያገለግሉትን 14ቱን ቅዳሴዎች በዜማ ተናገረ። ቅዳሴውን በዜማ የተናገረበት ቦታ መደባይታብር ይባላል። ይህም መደባይታብር የሚባለው ቦታ ለአክሱም ሰሜን ሆኖ ከአክሱም ግማሽ ቀን ያህል በእግር ያስኬዳል። ከዚያም ወደ ሰሜን ተራራዎች ወደ ጠለምት ሔዶ ምዕራፍ የተባለውን የዳዊትን መዝሙር ተናገረ። ከዚህ በኋላ ወደ ወገራና ወደ አገው እየዞረ ካስተማረ በኋላ ከሰሜን ተራራዎች ሥር ባሉት በአንዱ ገዳም ውስጥ በብሕትውና ከቆየ በኋላ በሰሜን ምሥራቅ ባለው ሸዋ ውስጥ በ571 ዓ/ም ግንቦት 11 ቀን አረፈና ተቀበረ።

ከዚህ በኋላ የእርሱ ደቀመዛሙርት ሳዊሮስና ሳንድሮስ በልዳዶስ የሚባሉት ከርሱ የተማሩትን የዜማ ባሕልና ሥርዓት በትግሬና በሰሜን አውራጃ እየተዘዋወሩ በየገዳማቱ ሁሉ ስለአስተማሩ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንቶ ይኖራል።

ምንጭ:“የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የዜማው ምልክቶች” ግንቦት 15/ 1959 በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የታተመ መጽሐፍ

በገና

አሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ !!! መዝ.፻፵፫፥፱

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ መሰረት ሶስት ዓይነት የዜማ ዓይነቶች አሉ

እነሱም ግዕዝ እዝል እና አራራይ ናቸው ፡፡

እነዚህ ዜማዎች ከሚዜሙባቸው የመዝሙር መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ በገና ነው ንጉሥ ዳዊት በበገና ደርዳሪነቱ እጅግ የተመሰገነ ነበረ “ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር ። ” ፪ሳሙ. ፮፥፭ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደምናገኘው በገናን የሚደረድሩ ከሌዊ ወገን እንዲሆኑ ያደረገውም ቅዱስ ዳዊት ነው “ ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ ። ” ፩ዜና. ፲፭፥፲፮ እስራኤላውያን ግን በገናን በመተዋወቅ ከዓለም ቀዳሚ ሕዝቦች ናቸው ፡፡ በእስራኤላውያን ዘንድ በገናን የሚደረድሩ የተለየ ክብር እና ቦታ እንደ ነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ፡፡ “ የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ ። ” ዘፍ. ፬፥፳፩

በገና ለእግዚአብሔር ማመስገኛነት እንዲውል እና በገና የሚደረድሩትም በቅዱሳት በዓላት ላይ በተለየ ቦታ እንዲቆሙ ሥርዓት የሰራው ቅዱስ ዳዊት ነው “ ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ ። ፪ዜና. ፳፱፥፳፬‐፳፮
በገናን በመደርደር እና እግዚአብሔርን በማመስግን ከርኲስ መንፈስ ከደዌ መፈወስ ይቻላል “ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው የሳኦልም ባሪያዎች እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት ። ሳኦልም ባሪያዎቹን መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው ። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ እነሆ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው በነገርም ብልህ መልኩም ያማረ ነው እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ ። ” ፩ሳሙ. ፲፬፥፲፮‐፲፰

በእስራኤላውያንም ሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በገና ለጸሎት ማቅረቢያ እንጠቀምበታለን በተላይ ወደ ተመስጦ በመውሰድ በእንቃእዶ ልቦና ጸሎትን ወደ እግዚአብሔር ለማደረስ በገናን የሚያክል መሳሪያ የለም “ እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው ልዑል ሆይ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ በማለዳ ምሕረትን በሌሊትም እውነትህን ማውራት አሥር አውታር ባለው በበገና ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ ። ” መዝ. ፺፩፥፫
በጥንተ እስራኤላውያን ታሪክ በገናንን ለአዋጅ ማስነገሪያነት እና ለደስታ መግለጫነት ይጠቀሙበት ነበር “ አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ የመለከትንና የእንቢልታን የመሰንቆንና የክራርን የበገናንና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል ። ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ። ” ዳን. ፫፥፬‐፮

እስራኤላውያን ልዑል እግዚአብሔር አምላክ ከፈተና ባዳናቸው ከአደጋ ሲታደጋቸው እግዚአብሔርን በበገና ያመሰግኑ ነበር “ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ ። በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ ። ” ፪ዜና. ፳፥፳፯‐፳፰
በገናን የሚደረድሩ ሌዋውያን ካህናት መስዋዕተ ኦሪት ሲያቀርቡ አብረው በበገና እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር “ መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በመሥራቅ በኩል ቆመው ነበር ። ” ፪ዜና ፭፥፲፪

እስራኤላውያን በሚያደርጓቸው ትልልቅ ግብዣዎች ወይም የልደት በዓላቸው ላይ በገናን በመደርደር የታወቁ ነበሩ “ መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም እጁም ያደረገችውን አላስተዋሉም ። ” ኢሳ. ፭፥፲፪

ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ወደ ሰማያት በተነጠቀ ከሰማቸው የምስጋና ድምፆች አንዱ የበገና ድምፅ ነበር “ እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ ። ” ራእ. ፲፬፥፪ በተመሳሳይ መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ ቅዱሳት መላእክት እግዚአብሔርን በበገና እንደሚያመሰግኑ እንዲህ ሲል ገልፆታል “ መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው ። መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ ። ” ራእ. ፭፥፰

በዓለም የረጅም እድሜ ባለ ፀጋ የመዝሙር መሳሪያ የሆነው በገና በኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ በእድሜው አቻ የለውም ፡፡ በገና በእጅ ከሚከረከሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ሲሆን የሚሰራው ከእንጨት እና ከእንስሳት ተዋፅኦ ነው ፡፡ ሳጥኑ አምዶቹ በርኩማው ከእንጨት ሲሰሩ አውታሮቹ ደግሞ ከከብት ጅማት ወይም ከከብት አንጀት ይሰራሉ ፡፡ የበገናዎች አውታሮች ቁጠር አስር እንዲሆን የተደረገው መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ነው “ እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት ። ” መዝ. ፴፪፥፪ የድሮ በገናዎች ሳጥኑ በክብት ቆዳ ሲሸፈን አሁን አሁን ደግሞ በእንጨት ውጤት ይሸፈናል ፡፡ በገና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን የተለያዩ የኢትዮጵያ ነገሥታት በገና ይደረድሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግት ያስረዳሉ ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስ እና አፄ ምኒልክ በገና ይደረድሩ ነበር ፡፡ በዚህ ዘመን በተለይ በገናንን በሚገርም የአደራደር ስልት በመደርደር በዓለም ዘንድ በሚገባ በማስተዋወቅ እንዲሁም በገናን ጠብቀው ካቆዩን መካከል ባለ ውለተኞቻችን መካከል እጅግ የማደንቃቸው መጋቢ ስብሐት ዓለሙ አጋ በጣም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ፡፡

የበገና ምሳሌዎች

በገና የእመቤታችን ምሳሌ ነው ፡፡

የሚያወጣው ድምፅ ደግሞ በእመቤታችንን ጣዕም እና ፍቅር ይመሰላል ፡፡
አስሩ አውታር በአስሩ ቃላተ ኦሪት ይመሰላል
በቀኝ እና በግራ ያሉት ሁለቱ አምዶች ደግሞ በቀኝ ያለው በፍቅረ እግዚአብሔር ሲመሰል በግራ ያለው አምድ ደግሞ በፍቅረ ቢጽ ይመሰላሉ ፡፡
በሌላ መልኩ በግራ ያለው አምድ የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ሲሆን በቀኝ ያለው አምድ ደግሞ ሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ነው ፡፡
ከእንጨት መሰራቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት መሰቀሉን ያመለክታል ፡፡
በገና ይህን ያህል ታሪክ ያለው ንዋየ ቅዱሳት ቢሆንም አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው እንደውም ከጥቂት አመታት በፊት ወደ መጥፋቱ ተቃርቦ ነበር ከተወሰኑ አመታት ወዲህ ግን በርካታ ወጣቶች በገናን ሲደረድሩ መመልከት እየቻልን ነው ለዚህ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን የበገና ድርደራ ትምህርት ክፍል በመክፈት ኦርቶዶክሳውያን እንዲማሩ እያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ የበገናንን የመጥፋት ስጋት በተወሰነ መልኩ ታድጓል ይህ መልካም እና የተቀደሰ ጥረት ግን በሁሉም አካላት ሊታገዝ ይገበዋል ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ላደረገው መልካም ስራ ሊመሰገን ይገባዋል ፡፡ እኛም በገናን መደርደር በመማር እግዚአብሔርን እናመስግን ይህንን ድንቅ የእግዚአብሔር ማመስገኛ ቅዱስ እቃ ለተተኪ ትውልድ እናስተላልፍ !!!

“ እግዚአብሔርን በመለከት ድምፅ አመስግኑት በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት ። ” መዝ. ፻፭፥፫

“ እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው ልዑል ሆይ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ በማለዳ ምሕረትን በሌሊትም እውነትህን ማውራት አሥር አውታር ባለው በበገና ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ ። ” መዝ. ፺፩፥፫

“ እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት ። ” መዝ. ፴፪፥፪

ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን

ቤተክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ የምታደርገን የልዑል እግዚአብሔር ደጅ ናት፡፡ /ዲድስቅልያ/

በሃይማኖት ሙቀት ቤተክርስቲያንን ያሞቃት የመንፈስ ቅዱስ እሳት ነው፡፡
/አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ/

የሙታን ትንሳኤ፣የዕውራን መሪ፣ትንቢተ ነቢያት፣ ስብከተ ሐዋርያት፣ክብረ ሰማያት፣ የጻድቃን ሞገስ፣ የደናግላን ንጽሕና፣ የቤተክርስቲያን መሠረት፣
መስቀል ነው፡፡
/ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

የቤተክርስቲያን ሕይወት በመስቀሉ ላይ ነው ስለኾነም ፈተና ይበዛበታል፡፡

ስለዚህ ከግል ሕይወታችኹ ይልቅ የቤተክርስቲያናችኹን አቋም አጠናክሩ፡፡
/አቡነ ጎርጎርዮስ/

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በምን ይለያል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በምን ይለያል?

1.ትንቢቱ የተረጋገጠ እውነት በመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በመረጣቸው ነቢያት የራሱን አምላካዊ ፈቃድ የገለጠበት ፍጻሜውንም በወሰነው ጊዜ እንዳከናወነ የተመዘገበበት ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋና የፍጻሜ መጽሐፍ ነው፤ በብሉይ ኪዳን አዶናይ ለሕዝቡ የሰጠውን ተስፋ በአዲስ ኪዳን ፈጽሟልና፡፡ በብሉይ ኪዳን በትንቢት የተነገሩት ከሰው አእምሮ እና ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የሆኑት አምላካዊ እቅዶች በአዲስ ኪዳን በትክክል ተፈፅመዋል፡ “ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” የሚለው የትንቢት ቃል ለተርጓሚው ለስምዖን አረጋዊ አእምሮ ቢከብድም ጌታ እንደቃሉ ከድንግል ማርያም ያለ ወንድ ዘር በመወለድ ፈጽሞታል፡፡ ኢሳ. 7፡14፤ ማቴ. 1፡23፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገሩ የትንቢት ቃሎች ለጸሐፊዎች ቢከብዱም ተፈጽመዋል፡፡ ያልተፈጸሙትም በጊዜያቸው ይፈጸማሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜ ያገኙና ያላገኙ ትንቢታትመዝገብ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ስለሚሆነው በእርግጠኝነት የሚናገር ብቸኛ መጽሐፍ ነው፡፡ መዝ. 49፡2



2. ስለፍጥረታት አፈጣጠር በእርግጠኝነት ስለሚናገር፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረታት አፈጣጠር ሲናገር በመላምታዊ አመክንዮ አይደለም፤ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ በማለት በእርግጠኝነት ይናገራልና፡፡ ዘፍ. 1፡1፡፡



3. የሰው ፈጠራ (ልብ-ወለድ) ባለመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የጠቢባን ምርምር ውጤት የሆነ ፍልስፍና፤ የደራሲያን የምጥ ፍሬ የሆነ ልብወለድ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነትና ጥረት የደረሱት የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መግባቢያ ቋንቋና ፊደል የተጻፈ ቢሆንም እንኳ ቃሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ኤር. 1፡9፤ ዘካ. 6፡9፤ዮሐ. 2፡22፤ ራዕ. 20፡12፡፡



4.በእግዚአብሔር መንፈስ የተመሩ (የተነዱ) ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት በመሆኑ፡-መጽሐፍ ቅዱስ የተለዩና የተመረጡ ሰዎች የጻፉት ቅዱስ መጻሕፍት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የቅድስና ጥሪ ሰምተው፣ በበጉ ደም ተዋጅተው፣ በፈቃዱ ተመርተውና በኑሮ ሥርዓታቸው አክብረውት ያረፉ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን ያጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ 2ኛጴጥ. 1፡20፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተመረጡ ጣቶች የተጻፈ ምርጦችንም የሚያፈራ አምላካዊ ቃል ነው፡፡



5. ዘመን የማይለውጠውና የማይሽረው በመሆኑ፡- ብዙ መጻሕፍትን ዘመን ሽሯቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡ በዘመን ብዛት የተረሱ በርካታ መጻሕፍት አሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በየዘመናቱ እጅግ ተፈላጊ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተረሳውን የሚያስታውሰው አምላክ ቃል በመሆኑ አይዘነጋም፤ በየጊዜው ተሽሎ ለሚነሳው ትውልድ የሕይወት ሥርዓት መሪ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና፡፡ ኢሳ. 40፡8፡፡



መጽሐፍ ቅዱስ በየዘመናቱ የገጠሙትን የአመለካከት ጽንፎችና የኢ-አማንያንን ጦርነቶች አልፎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረው አምላካዊ ቃል ስለሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብርቱ ተቃውሞዎችን አልፎ ለዚህ ትውልድ የደረሰው እግዚአብሔር በረዳቸው የታመኑ ምስክሮች መስዋእትነት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመን የማይሻርና በትውልድ የማይሻሻል ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም መጻሕፍት በላይ የእድሜ ባለጠጋ (አረጋዊ) ነው፡፡



6. ለሁሉም የሚናገር መጽሐፍ ስለሆነ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ድሀና ሀብታም፣ የተማረና ያልተማረ፣ ትንሽና ትልቅ ሳይልሁሉን በየአድራሻው ይናገራል፡፡ ፊት አይቶ የማያደላው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የላከው የፍቅር ደብዳቤ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስማንነትን በግልጥ በስልጣን ቃል ይናገራል፡፡



7. የሚያነቡትንና የሚሰሙትን የሚባርክና የሚያንጽ በመሆኑ፡- በዓለማችን አንባቢያንን የሚያንጹ መጻሕፍት ሊኖሩቢችሉም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ውስጣዊ ማንነትን የሚሠራ መጽሐፍ የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የሕይወት መምህር ነው፡፡ አንባቢያንና ሰሚዎች ከመታነጽ አልፈው የሚባረኩበትም መጽሐፍ ነው፡፡ መዝ. 22፡4፣ 2ጢሞ. 3፡17፣ ራዕ. 1፡3፡፡መጽሐፍ ቅዱስ የሚያንጻቸውና የሚባርካቸው የታላቅነትን ምስጢር በማወቅ ስኬትን ይጎናጸፋሉ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ “የእንግሊዝ አገር ታላቅነት ምስጢሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የታላቅነትን ምስጢር እንደሚያጎናጽፍ መስክራለች፡፡



8. የሁሉ ምንጭ በመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖትና የስነ-ምግባር፣ የኪነጥበብና የስነ-ጽሁፍ፣ የሥራ-አመራርና የፍትሕ፣ የግብርናና የጤና፣ የእውነተኛ መጻሕፍትና የእውነተኛ ትምህርቶች ምንጭ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ባለመጥፋት ከሚወዱት ጋር ይሁን!!

አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር

አንትሙሰ ሶበት ጸልዩ ስመ ዝበሉ፡፡” ማቴ.6፥

እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በላችሁ ጸልዩ “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

“አንትሙሰ ሶበት ጸልዩ ስመ ዝበሉ፡፡” ማቴ.6፥

እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በላችሁ ጸልዩ “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን….

በዚህ የጸሎት ክፍል ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ81 መጻሕፍት የተገኙ አምስት ቁም ነገሮችን አስተምሯል፡፡

ሃይማኖት

ተስፋ

ፍቅር

ትሕትና

ጸሎት

1. ሃይማኖት፡- ሃይማኖት ማለት በዐይናችን ያላየነውን አምላክ አባታችን ሆይ ሲሉ መኖር ነው ቀደም ሲል የነበሩ አበው ነቢያት ሲጸልዩ እግዚእነ አምላክነ ንጉሥነ እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ ይህም ከግብርናተ ዲያብሎስ /ለዲያብሎስ ከመገዛት/ እንዳልዳኑ ለማጠየቅ ነው፡፡ እኛን ግን ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ አውጥቻችኋለሁ ሲል አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ አስተማረን፡፡ “ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ” /ገላ.4፥6፣ ሮሜ.8፥15/፡፡ አባትነቱንም በሁለት ነገር ከምድራዊ አባት ለይቶታል፡፡

በመውለድና በመግቦት ከምድራዊ አባት ይለያል፡፡ ምድራዊ አባት በዘር በሩካቤ ይወልዳል፡፡ በማር፣ በወተት፣ በፍትፍት ያሳድጋል፤ ኋላም በሞት ሲያልፍ የምታልፍ ርስትን ያወርሳል፡፡ እርሱ ግን ሲወልደን በርቀት ሲያሳድገንም በሥጋውና በደሙ ነው፡፡ “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው ዮሐ. 3፥6፡፡ ኋላም የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን “በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን” ኤፌ.1፥11፣ 1ኛጴጥ.3፥5፡፡ በአበው ነቢያት ሐዋርያትን፣ በሐዋርያትም እኛን አቅርቦ አባታችን ሆይ ብለን እንድናመሰግነው አዞናል፡፡

ምድራዊ አባት የሚመግበው እግዚአብሔር ስለሚሰጠው ለልጁ በመስጠት ተቀብሎ በማቀበል ነው፡፡ እርሱ ግን መመገብ የባሕርዩ ስለሆነ ከሌላው ነስቶ አይደለም፡፡ ምድራዊ አባት ሲያጣ አጣሁ ይላል እርሱ ግን አያጣም፡፡ ምድራዊ አባት ሰጥቶ ሲያልቅ አለቀ ይላል፡፡ የእርሱ ግን ስጦታው አያልቅም፡፡ “በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የሚያረጁትን ኮረዶች ለራሳችሁ አድርጉ” ሉቃ.12፥33፡፡ ምድራዊ አባት ከትልቁ ልጁ ይልቅ ለትንሹ የደላል እርሱ ግን ዓለምን በእኩል ምግብና ይመግባል፡፡ ምድራዊ አባት ትዕዛዙን ካልተጠበቀለት ልጁን ከቤት ያስወጣል፣ ያባርረዋል እርሱ ግን ሁል ጊዜ በትዕግስት ይመለከተናልና፡፡ “በጻድቃንና ለኀጥአንም ዝናምን ያዘንማልና” ማቴ.5፥45፡፡ እኛ አባትነቱን አምነን አባታችን ሆይ ብንለው እኛ ልጆቹ መሆናችን የልጅነት ሥልጣን እንዳገኘን እንመሰክራለን፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” እንዲል ዮሐ.1፥12፡፡ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ 1ዮሐ.3፥1፡፡

ከላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስረዱን የእግዚአብሔር ፍቅር ከምድራዊ አባት የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ምድራዊ አባት ልጁን ቢወደውም ሥልጣን አይሰጠውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለልጆቹ አጋንንትን እንዲያወጡ ድውያንን እንዲፈውሱ ለምጽ እንዲያነጹ ሙታን እንዲያስነሡ ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ “አሥራ ሁለቱን ደቀመዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው” እንዲል ማቴ.10፥1፡፡

በመኖሪያው /በሰማያት/ በመኖሩ ከምድራዊ አባት ይለያል፡፡ በሰማያት የምትኖር ብሎ በመኖሪያው ከምድራዊ አባት ለይቶታል፡፡ አሁን እግዚአብሔር በምድር የሌለ በሰማይ ብቻ የተወሰነ ሆኖ አይደለም በሰማይም በምድርም የመላ አምላክ ነው፡፡ “ከመንፈስ ወዴት እሔዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ ወደጥልቅም ብወርድ በዚያ አለህ፡፡ እንደንስር ክንፍን ብወስድ /ቢኖረኝ/ እስከባሕር መጨረሻም ብበርር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፡፡” መዝ.139፥7 በማለት ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ እንደሌለ ገልጿል፡፡

በሰማያት የምትኖር በሉኝ ያለን ብዙ ጊዜ መገለጫው፣ መቀመጫው፣ ለቅዱሳን እርሱ በወደደ እነርሱ በሚችሉት መጠን የተገለጠና የታየ በሰማይ ስለሆነ ነው፡፡

“ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀመጦ አየሁት የልብሱን ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር” ኢሳ.6፥1-6፡፡

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መርገጫ ናት” ኢሳ.66፥1፡፡

ኢሳይያስ ምልአቱን፣ ክብሩን፣ ልዕልናውን በአየው መጠን ነገረን፡፡ ይህን የአገልጋዩ የኢሳይያስን ምስክርነት ሳይለውጥ ነቢያት የተናገሩልኝ የስተማሩልኝ፣ የሰበኩልኝ እኔ ነኝ በማለት እነ “ኢሳይያስ ሰማይ ዙፋኔ ነው” ያለውን እንደአስተማሩ እርሱም በሰማያት የምትኖር ብላችሁ አመስግኑኝ አለን፡፡ ስለ ልዕልናው ስለ ክብሩ በሰማይ አለ ይባላል፡፡ “በእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት” እና ትርጓሜ ወንጌል “ስለ ልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ” ከዚህም የተነሣ ጌትችን ሲያስተምር “በሰማያ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና በምድርም አትማሉ የእግሩ መረገጫ ናትና” ማቴ.5፥32 ብሏል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌቶችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአየው ጊዜ እንዲህ መስክሯል “ወደሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና እነሆ ሰማያት ተከፍታው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ” ሐዋ.7፥55፡፡

ስለዚህ ብዙ ጊዜ በሰማይ ለወዳጆቹ ከመገለጡ የተነሣ አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ብላችሁ አመስግኑኝ አለን፡፡

2. ተስፋ፡- ተስፋ ማለት የወደፊት አለኝታ እናገኘዋለን ብለን የምንጠብቀው መከራ የምንቀበልለት፣ በዚህ ዓለም ባይመቸን መከራ ቢጸናብን፣ ብንገፋ ብንከፋ ብናዝን ብንጨነቅ ያልፋል ብለን የምንጽናናበት ነው፡፡ ይህን ተስፋ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡ “በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም” ሮሜ.5፥2-5 ተስፋ ከላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ሰማዕታት ከነደደ እሳት ገብተው፤ የተሳለ ስዕለትን ታግሰው፤ የዓላውያን ነገሥታትን ግርማ አይተው ሳይደነግጡ፣ ሃይማኖታቸውን ሳይለውጡ፣ ሹመቱን ሽልማቱን ወርቁን ብሩን ምድራዊ ክብራቸውን ትተው መከራ የተቀበሉት ለተስፋ መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ጻድቃንም ድምጸ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ፍትወታት እኩያትን ታግሰው፣ በምናኔ በተባሕትዎ ከዘመድ ባዳ ከሀገር ምድረ በዳ ይሻለናል ብለው የኖሩት ለዚሁ ተስፋ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጴጥሮስ በሃይማኖት ምክንየት ተበትነው ለነበሩ ምዕመናን ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል፡፡ “እስመ በእንተ ዝንቱ ተጸዋእክሙ ከመ በረከተ ትረሱ በእንተ ዛቲ ተስፋክሙ” ለዚች ተስፋችሁ መከራን ትቀበሉ ዘንድ ተጠርታችኋልና 1ጴጥ.2፥22 የህ ተስፋ መጻሕፍት የተባበሩበት ነው” በተስፋ ያጽናናልና ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን” ሮሜ. 8፥24፡፡ ስለዚህ ተስፋ የምንለው የማናየውን መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ይህን ተስፋ በጸሎታችን ውስጥ መንግሥትህ ትምጣ ብለን እንድንለምን ጌታችን አስተማረን፡፡ አሁን መንግሥትህ ትምጣ ስንል መንግሥተ ሰማያት ክንፍ ኖሯት በራ፣ እግር ኖሯት ተሽከርክራ የምትመጣ ሆኖ አይደለም ትሰጠን በሉኝ ሲል ተስፋ የምናደርጋት መንግሥትን እንዲያወርሰን ለምኑ አለን፡፡

3. ፍቅር ፡- ፍቅር ማለት አንዱ ለሌላው መጸለይ ነው፡፡ ይኸውም “የዕለት ምግባችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው ነው፡፡ ሰው ሁሉ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ሲጸልይ የዕለት እንጀራዬን ሰጠኝ ብሎ” አይጸለይም ለጠላቶቹም ለወዳጆቹም ጠቅላላ ሰው ሆኖ የተፈጠረ የተፈጥሪሮ ወንድምና እኅት ሁሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእገሌ የሚል አደለም፡፡ ጠቅል አድርጎ የዕለት ምግባችንን ስጠን የሚል ነውና፡፡ ይህ ፍቅር ነው ሊቃውንት በትርጓሜያቸው ይህን ሲተረጉሙት ዕለት ዕለት እንድንማር፣ ሥጋውን ደሙን እንድንቀበል፣ ንሰሓ እንድገባ አድርግ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ከምግበ ሥጋ ያለፈ ጸሎት ነው፡፡ ይህም ጸሎት ለሕዝቡ ለአሕዛቡ ለጠላት ለወዳጅ ለዘመድ ለባዕድ ሳይባል ለሁሉም የሚጸለይ ጸሎት ሲሆን እግዚአብሔር እኛን እንደወደደን እርስ በእርሳችንም እንዋደድ ዘንድ ተዋደዱ “ጠላቶቻችሁንም ውደዱ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ” ብሎ አስተምሮኗል፡፡ ለሁሉም የሚሆን የጸሎት ፍቅርን የሚገልጽ ጸሎት “የዕለት ምግባችንን ስጠን” በሉኝ አለን፡፡

4. ትሕትና፡- ትሕትና ማለት ራስን ዝቅ ማድረግ ማዋረድ ከሁሉ በታች ማድረግ ትዕቢትን ኩራትን ትዝህረትን ማስወገድ ነው፡፡ “ትዕቢትን ግን አታስቡ ራሲን የሚያዋርደውን ሰው ምሰሉ ሮሜ.12፥16፡፡ ይህም “ኀጢአታችንን ይቅርበለን” የሚለው ነው ይህን ጸሎት የበቃውም ያልበቃውም ይጸልየዋል፡፡ የበቃው የነጻው ከኃጢአት አልፎ ከአስረኛው መዓርግ የደረሰው ሁሉ ይጸልየዋል፡፡ ይህንን ሲጸልይ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ከእኛ መደብ ውስጥ አስገብቶ ኀጢአታችንን ይቅር በለን ይላል፡፡ እርሱ ግን ከኀጢአት አልፎአል ስለትሕትና እኛን መስሎ እንደኛ ሆኖ ይጸልየዋል፡፡ ጌታችን ብዙ ጊዜ ስለትሕትና አስተምሯል፣ “እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው” ማቴ 18፥4 “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ማቴ 20፥26-28፡፡

“ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” ማቴ 23፣11 እነዚህና ጌታችን ያስተማራቸውን በተግባር የሚያውሉ ቅዱሳን በቅተው ሳለ እንዳልበቁ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ይጸልያል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደተማረው የትሕትና ጥቅምን ጽፎአል “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኀይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” 1ጴጥ 5፥6፡፡ በዚህ ጸሎት ውስጥ ይህ ጠቃሚ የሆነ ጸሎት ተአምኖ ኀጣውእ (ኀጢአትን ማመን) ያለበት በደላችንን ይቅር በለን የሚለው ትሕትና ነው፡፡

5. ጸሎት ፡- ጸሎት አባታችን ሆይ ብሎ እስከ መጨረሻው ያለው ነው አባችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥት ትምጣ ፈቃድ ይሁንልን ይደረግልን የዕለት እንጀራችንን ስጠን በደላችንን ይቅር በለን ጸሎት ነው ታዲያ ይህን በንባብ አጭር በምሥጢር ጌታ መጻሕፍት ያጠቃለለ ታላቅ ጸሎት አፍ ንባብ ይነዳ ልብ ጓዝ ያስናዳ እንዲሉ አበው ኅሊናን በማባከን ሳይሆን በንቃት፣ በትጋት ሆነን ብንጸልይ እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ነው ክብር ምሥጋና ይግባውና አባታችን ሆይ ብላችሁ ጸልዩ ያልን፡፡

22ቱ የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች

22ቱ የእግዚአብሔር ኅቡዕ ስሞች መዝሙረ ዳዊት 118


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

22ቱን ሥነ-ፍጥረት ምሳሌ በማድረግ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ኅቡዕ ስሞች እንደሚከተለው በዝሙሩ አመስግኖታል። በመዝሙረ ዳዊት 118

1. አሌፍ ፡ ዓለምን ከነጓዟ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ እግዚአብሔር ማለት ነው።
2. ቤት፡ እግዚአብሔር ሁሉን መስጠት የሚችል ቸር ለጋስ ባለጸጋ ማለት ነው።
3. ጋሜል፡ እግዚአብሔር ሊመረመር የማይችል ግሩም ድንቅ ማለት ነው።
4. ዳሌጥ፡ እግዚአብሔር በጌትነቱ ዙፋን ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
5. ሄ፡ እግዚአብሔር በአንድነቱ በሦስትነቱ ለዘለዓለም ይኖራል ማለት ነው።
6. ዋው፡ እግዚአብሔር በመንግሥት በሥልጣን በአገዛዝ በባህርይ አንድ አምላክ የሆነ ማለት ነው።
7. ዛይ፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ እየታሰበ ሲመሰገን የሚኖር ፈጣሪ ማለት ነው።
8. ሔት፡ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ሽረት በባሕርዩ ኅልፈት የሌለበት ለዘለዓለም ሕያው የሆነ ማለት ነው።
9. ጤት፡ እግዚአብሔር ጥበብን የሚገልጽ ከጥበበኞች ይልቅ ጥበበኛ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
10. ዮድ፡ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ እሱ ኃያልና ጽኑዕ የሆነ ማለት ነው።
11. ካፍ፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የሌለ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው አምላክ ማለት ነው።
12. ላሜድ፡ እግዚአብሔር ልዑለ ባሕርይ የሆነ ማለት ነው።
13. ሜም፡ እግዚአብሔር ንጹሕ ባሕርይ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
14. ኖን፡ እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ የገዥዎች ገዥ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
15. ሳምኬት፡ እግዚአብሔር ሁሉን የሚገዛ አምላክ ማለት ነው።
16. ዔ፡ እግዚአብሔር ታላቅና ገናና የሆነ አምላክ ማለት ነው።
17. ፌ፡ እግዚአብሔር ተወዳጅ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
18. ጻዴ፡ እግዚአብሔር ሐሰት የሌለበት እውነተኛ አምላክ ማለት ነው።
19. ቆፍ፡ እግዚአብሔር ለልበ ቅኖችና ለየዋሃኖች ቅርብ የሆነ አምላክ ማለት ነው።
20. ሬስ፡ እግዚአብሔር ክብሩ ከእርሱ ለእርሱ የተገኘ የሁሉ ጌታ ማለት ነው።
21. ሳን፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ የተመሠገነ ማለት ነው።
22. ታው፡ እግዚአብሔር እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ፤ ድካም የማይሰማው ጽኑዕ የሆነ ፈጣሪ ማለት ነው።

ሐዘን ሲገጥመን ምን እናድርግ?

ሐዘን ሲገጥመን ምን እናድርግ?

ሐዘን ሲገጥመን ምን እናድርግ? / 2ቆሮ 5÷1-5 /

ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

የምንወደው ሰው በሞት ከእኛ ሲለይ በእጅጉ እናዝናለን፤ እናለቅሳለንም፡፡ በርግጥም ማልቀስ በአግባቡ ከሆነ ጠቃሚና አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በመሪር ሐዘን የተቆጣውን ሰውነታችንን የሚያስተነፍስ መፍትሔ፤ዕንባ፡፡ የውስጥ ሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ቋጥሮበት ወይም በእግርና በእጁ ላይ መግል የቋጠረ የቁስል ጥዝጣዜ ዕረፍት የነሣው ሰው የቋጠረውን ፈሳሽ ወይም የሚጠዘጥዘውን መግል ሲያፈሱለት ደስ እንደሚለውና ዕረፍት እንደሚሰማው በሐዘን ውስጡ የተጎዳ ሰውነትም ዕንባ ሲያፈስ ዕረፍት ማግኘቱ አይቀሬ ነው፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ዕንባ እንዲኖረው አድርጎ የፈጠረውም ዕንባ ጠቃሚና አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ እስከ አሁን በምናውቀው እንኳ ሦስት ከፍተኛ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

የመጀመሪያው ጠቀሜታው ዕንባ በሰው ልጅ ታሪክ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ያለው ነው፡፡ ዕንባ የተጀመረው በአዳምና በሔዋን ነው፡፡ ያለቀሱትም አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በልተው እግዚአብሔርን በመበደላቸው ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ የተጀመረው በንስሐ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ከዚያ በፊት በሰውነታቸው ያልነበረ ነገር ተፈጠረ ማለት አይደለም፡፡ በሩካቤ መተዋወቃቸውን /የተዋወቁበትን ጊዜ/ ይዘን በዚያ ጊዜ የመራቢያ ብልታቸው ተገኘ እንደማንለው ዕንባውም እንዲሁ ነው፡፡ በቀሌምንጦስ «አልቦቱ ካልዕ ሕሊና ለአዳም ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ፤ ለአዳም ስለ ኃጢአቱ ከማልቀስ /ኃጢአቱን እያሰበ ከማልቀስ/ በቀር ሌላ አሳብ /ግዳጅ/ አልነበረውም» ተብሎ እንደተጻፈ ዕንባ የተጀመረው በዚህ ነው፡፡ ስለዚህ የዕንባ ቀዳሚ ጠቀሜታ ሰውን በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ ተመዝግቧል፡፡ «ወበአንብዕየ አርሐስኩ ምስካብዬ፤ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ» የሚለው ቅዱስ ዳዊት የንስሐ ዕንባውን፣ የጸሎት ዕንባውን ነው፡፡ /መዝ 6÷6/ ጌታችንም በወንጌል «ብፁዓን እለ ይላህው ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌስሑ፤ ዛሬ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ የተመሰገኑ ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ 5÷4/ ሲል ያስተማረው የሚገባው ለቅሶ ወይም ዕንባና ሐዘን የንስሐ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ በሌላም ቦታ «እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፣ ታዘናላችሁና፣ ታለቅሱማላችሁ» /ሉቃ 6÷25/ ሲል ያስጠነቀቀን ጠቃሚውን ዕንባና ሐዘን ለማስተማር ነው፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም «ከሳቅ ሐዘን ይሻላል፣ ከፊት ኀዘን የተነሣ ደስ ይሰኛልና፤ የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት [በንስሐ] ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት [ኃጢአት በሚፈጸምበት ቦታ] ነው» በማለት የንስሐ ዕንባን መፈለግ ጠቢብነት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ከዚህም በላይ በቅድስና ሕይወት የሚኖሩ ቅዱሳን በዐሥሩ መዓርጋት ሲሸጋገሩ አራተኛው መዓርግ አንብዕ ይባላል፡፡ ይህም ፊታቸው ሳይከፋውና ሰውነታቸው ሳይሰቀቅ ዕንባን ከዓይናቸው ማፍሰስ ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ ይህን የመሰለ ጠቀሜታ ያለው በመንፈሳዊነትም የብቃት ደረጃ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ጠቀሜታው ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በዓይኑ ላይ ሁልጊዜም ስስ የሆነች የዕንባ ሽፋን አለችው፡፡ ሳይንስም ጭምር እንደ ተረጋገጠው ዓይንን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠብቁት ነገሮች አንዷና ዋናዋ ይህች ዕንባ ናት፡፡ ስለዚህ በነፋስ፣ በፀሐይ፣ ጨረርና በመሳሰለው ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስበት ይህች ዕንባ ትከላከልለታለች፡፡ በነፋስና በሙቀት ደርቃ እንዳታልቅም እግዚአብሔር በጥበብ እንድንጠቀምባት አድርጓል፡፡ ማንኛውም ሰው ዓይኑን ጭፍን አድርጎ ሲከፍተው በዓይኑ ላይ የነበረችውን ስስ የዕንባ ሽፋን ገፍቶ ወደ አፍንጫ በሚያወርደው ቀዳዳ ያስወግድና አዲስ ዕንባ ይተካል፡፡ በዚህ መንገድ በየደቂቃው ወይም ዓይናችንን ጭፍን ግልጥ ባደረግን ቁጥር ይህችን የዕንባ ሽፋን በአዲስ መልክ ስለምንቀይር ዓይናችንን በረቂቅ መንገድ እንጠብቃለን፡፡ የሀገራችን ሰው «የዓይን አምላክ» የሚለው ለዓይን ይህን የመሰለ ሰፊ የጥበቃ መንገዶችን እግዚአብሔር ስለፈጠረልን ነው፡፡ በመጽሐፍም «ዕቀበኒ እግዚኦ ከመ ብንተ ዓይን፤ አቤቱ እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ» የሚል ቃል ተጽፏል፡፡ ስለዚህ ዕንባ ዓይንን እንዲህ አድርጎ ለመጠበቅ ጠቃሚ ነው ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው ጠቀሜታው ደግሞ ሐዘንን ማስወገጃ ማስተንፈሻ የሐዘን ማቅለያ መሆኑ ነው፡፡ ከዛሬው የጽሑፋችን ዓላማ ጋር የሚገናኘውም ይኽኛው ነው፡፡ የመጀመሪያው አባታችን አዳም የመጀመሪያ ልጁ አቤል በሞተ ጊዜ እጅግ ተጨንቆ ሰውነቱ ሁሉ አባብጦ ተነፋፍቶም እንደነበር ትውፊቱን የመዘገቡ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ በመጀመሪያ ሞት ከዚያ በፊት አይታወቅምና ምን ማድረግ እንደነበረባቸው እንኳን አዳምና ሔዋን አያውቁም ነበር፡፡ ዳግመኛም በዚያ ጊዜ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በምድር ላይ እነርሱ ብቻ ናቸውና የሚያጽናናቸውም ሆነ የሚመክራቸው ሰው ማንም አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት አዳም ሰውነቱ በሐዘን ተዋጠ፤ ተጨነቀ፤ ሰውነቱም ተቆጣ፤ ታመመም፡፡ በዚህ ጊዜ መላእክት ወደ አዳም መጥተው እንዲያለቅስ አሳዩት፤ አስተማሩት፡፡ እርሱም ሲያለቅስ ውጥረቱ በረደ፤ የተቆጣ አካሉ ተመለሰ፤ ሰውነቱም ዕረፍት አገኘ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሐዘን የሚገጥመንን የሰውነት መታመምና ከባድ ጭንቀት በዕንባ መገላገሉን ይዘን ይኸው እስከ አሁን ዘልቀናል፤ ወደፊትም እንቀጥላለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አልዓዛርን ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ከሞት ሊያስነሣው ሲሔድ በእኅቶቹ ቤት እንደደረሰ መጀመሪያ አልቅሶለታል፡፡ /ዮሐ 11/፡፡ ይህም በሞት ለተለየን ሰው በሐዘን ጊዜ ማልቀስ ተገቢ መሆኑን ይህንም በማድረጋችን ኃጢአት እንደማንሠራ ያስረዳናል፡፡ ጌታ ቸር አምላክ፣ ሰውንም ወዳጅ ነውና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከሞት እንደሚያስነሣው እያወቀ እኅቶቹን ሲያገኛቸው መጀመሪያ ሐዘናቸውን በልቅሶ ተካፈለ፡፡ ከዚያም እነርሱን አጽናንቶ ሞቶ የተቀበረውን ከሞት አሥነሥቶ ከመቃብር አውጥቶታል፡፡ በዚህም እጅግ ብዙና ሰፊ ትምህርቶችን አስተምሮናል፡፡

ለክርስቲያኖች በሐዘን ጊዜ ማድረግ ስለሚገባቸውና ስለማይገባቸው ነገሮች መሠረታዊ የሆኑት የትምህርት መነሻዎች ከላይ የጠቀስናቸው እነዚህን የመሰሉት በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጡት ታሪኮች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በሞት ለተለየን ቤተሰባችን የተሰማንን ሐዘን በለቅሶና በዕንባ መገላገል ተገቢ ቢሆንም ለእነዚህም ጊዜና መጠን አላቸው፡፡

በጊዜ ያልተወሰነ በመጠን ያልተገደበ ከሆነ እንኳን ሐዘን፣ ለቅሶና ዕንባ ቀርቶ ደስታና ጨዋታም በእጅጉ ጎጂ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ሐዘንን በዕንባ መገላገል ጠቃሚና እግዚአብሔር የፈቀደው ቢሆንም ከመጠኑ ሲያልፍ ደግሞ ከጥቅሙ በተቃራኒ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ በበጋ የደረቀች መሬትን ለማርጠብ፣ ለማለስለስና እህሉንና ሣሩን ለማብቀል የክረምት ዝናም አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከመጠን በላይ ከወረደ ግን እርሻውን አጣጥቦ በመውሰድ፣ የበቀለውን አዝመራ በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ለቅሶና ዕንባም እንዲሁ ነው፡፡ ዓይንን ለመጠበቅና ሰውነታችን በሐዘን እንዳይጎዳ ለመከለካል የተፈጠረውን ዕንባ ስናበዛው ዓይናችንን ለማጥፋት፣ ሰውነታችንም ጎርፍ እንደበላው መሬት ሸርሸሮ ለማይድን በሽታ ያበቃዋል፡፡ ስለዚህ ልክና መጠኑን ጠብቆ በጊዜ ተወስኖ የሚፈጸም ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፣ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፡፡ የዓለም ሐዘን ግን ሞትን ያመጣል፡፡» /2ቆሮ 7÷10/ የሚለን ለዚህ ነው፡፡

አንድ ሰው ከቤተሰብ አንዱ በተለየው ጊዜ የሚያደርገው ነገር በመጠንና በሥርዓት ካልሆነ እንኳን ሥጋውን ነፍሱንም ጨምሮ ይጎዳዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዘናቸው ምክንያት እግዚአብሔርን ያሳዘኑ እርሱም ያዘነባቸው ሰዎች አሉ፤ እንዲሁም ደግሞ በሐዘናቸው እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ሰዎች አሉ፡፡ በወንጌል እንደተጻፈው የሰማዩን ቤት የማያስቡ፤ በጎ የሠሩ ሰዎች በሰማይ ከእግዚአብሔር የሚቀበሉትን በጎ ዋጋ ረስተው የሰውን ሞት ተስፋ እንደሌለው እንደ እንስሳ እና እንደ አራዊት ሞት ወይም ተቆርጦ እሳት በልቶት አመድ እንደሚሆን ካለበለዚያም ወድቆ በስብሶ አፈር ሆኖ እንደሚቀር እንደ ዛፍ እንደ ቅጠል ቆጥረው መሪር ሐዘን የሚያዝኑ ሰዎች ሰነፎች ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያሳዝናሉ፤ እግዚአብሔርም ያዝንባቸዋል፡፡ «ሙታናቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸው» ብሎ ጌታ በወንጌል የተናገረላቸው ሰዎች የሰውን ክብር እና የእግዚአብሔርን ኃይል ለማያውቁ ሰዎች ነው፡፡ እንደዚህ ያሉት ሰዎች «ሙታን» የተባሉት በምድር ላይ በሕይወት እየኖሩ ነው፡፡ ሙታን የተባሉት የሞተ ሰው ሥጋው ምንም ሊያውቅ እንደማይችል እነዚህም እየኖሩ የማያውቁና የማያስታውሱ ስለሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ትንሣኤ እንደሌለን በሰማይ በአባታችን ቤትም ክብርና ጸጋ እንደማይጠብቀን አድርጎ የሚያዝንና የሚያለቅስ ከሆነ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን እንደተጻፈውም ቆሞ የሚሔድ ነገር ግን የሞተ ይሆናል፡፡

በተጠቀሰው መንገድ እግዚአብሔርን ያሣዘኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ እግዚአብሔርን ያስደሰቱትም ደግሞ አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱና ዋናው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው ዳዊት ልጁ በታመመ ጊዜ በእጅጉ አዝኖ ነበር፡፡ ከሞተ በኋላ ግን ያደረገው ብዙዎችን አስገርሟል፤ አርአያነቱም ታላቅ ነው፡፡ ታሪኩን የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡ «እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሰፈ፣ እጅግም ታምሞ ነበር፡፡ ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፣ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ፡፡ የቤቱም ሸማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፣ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም፡፡ በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ፡፡ የዳዊትም ባሪያዎች ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን ?» በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ፡፡ ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደሞተ አወቀ፤ ዳዊትም ባሪያዎቹን ሕፃኑ ሞቶአልን? አላቸው፡፡ እነርሱም፡- ሞቶአል አሉት፡፡ ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፣ ተቀባም፣ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ፡፡ ወደ ቤቱም መጣ፣ እንጀራ አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም አቀረቡለት፣ በላም፡፡ ባሪያዎቹም፡- ይኽ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፤ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት፡፡ እርሱም፡- ሕፃኑ ሕያው ሳለ እግዚአብሔርም ይምረኝ፣ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁም፡፡ አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሔዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ፡፡» /2ሳሙ 12÷15-23/፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ንጉሡ ዳዊት ልጁን ምን ያህል ይወደው እንደነበር፤ ከዙፋኑ ወርዶ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ፤ ማቅ ለብሶ አመድ ነስነሶ በጾምና በጸሎት እንደ ተጋደለ እንመለከታለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሞተ በኋላ በሰማይ የሚደረገውን ስለሚያውቅ «እኔ ወደ እርሱ እሔዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመጣም» በማለት በሰማይ ቤት ያለውን ጽኑ እምነት፤ ሞተ ማለትም ወደ እግዚአብሔር ሔደ ማለት እንጂ ሌላ ማለት ስላልሆነ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሔዶ ሰግዶ፤ እግዚአብሔርንም አመስግኖ እንደተመለሰ ይነግረናል፡፡

በመጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈውን ስንመለከት ደግሞ በሐዘን ጊዜ እግዚአብሔርን እንዴት ማስደሰት እንደሚቻል እንረዳለን፡፡ ኢዮብ በአንድ ቀን ዐሥር ልጆቹ ሞተውበታል፤ በዚያው ቀንም ሊቆጠር የማይችል ሀብትና ንብረቱን አጥቷል፤ እርሱ ግን «እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ» አለ እንጂ አላማረረም፤ ሐዘኑንም በቅጡና በሥርዓቱ ተወጥቶታል፡፡ በዚህ ምድር ያለን ሰዎች ለሰው የማይቀረው ሞት አንዱ ቤተሰባችን ሲጠራው ከእኛ መካከልም በሞት ሲወሰድ ተመልክተን ይሆናል፡፡ እንደ ኢዮብ ግን ዐሥር ልጆቹ በአንድ ቅጽበት ያጣ ሰው የለም፡፡ በዚህም ከእግዚአብሔር እጥፍ ድርብ ዋጋ አገኘበት እንጂ አልተጎዳበትም፡፡ እንዲያውም ከቀደሙት የበለጡ ልጆች፣ ከቀድሞው ዕጥፍ ድርብ የሆነ ሀብት ተሰጥቶት፤ እንደተረገመ የቆጠሩት ሰዎች ሁሉ አፈሩ፤ እርሱ ግን በማጣቱም በማግኘቱም ጊዜ፤ በሐዘኑም በደስታውም ጊዜ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ ተባረከበትም፡፡ ታዲያ የሕይወታችን እውነታ እንዲህ ሆኖ ሳለ አንዳንዶቻችን ያለ መጠን የምናዝነው፣ የምንፈተነው እና የምንጨነቀው ለምንድን ነው ? እንደ ኢዮብ እንደ ዳዊት ለመሆንስ ለምን ተሳነን ?

«ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈረስ፣ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ፣ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን፡፡ ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው፣ እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን፡፡» /2ቆሮ 5÷1-5/