Wednesday, June 10, 2015

"መኖር እንዲህ ነበር"

"መኖር እንዲህ ነበር"
ገና ሲወለዱ ይችን ምድር ሲያዩ፣
የዓለምን ጣዕምና ምሬቷን ሳይለዩ፣
መኖር እንዲህ ነበር ጌታን ብቻ እያዩ።
ገና በማለዳ ገና በጠዋቱ፣
ገና ቀትር ሳይሆን ሳይመጣ ምሽቱ፣
ገና ሳይሰለጥን ጨለማው ሌሊቱ፣
ገና ብርሃን ሳለ ሥራን ሳይታክቱ፣
መኖር እንዲህ ነበር እንዲያርግ ጸሎቱ።
በዓለም ያለውን ዓለምን ሳይወዱ፣
ዓለምን አግብቶ ሌላ ዓለም ሳይወልዱ፣
መኖር ይሻል ነበር ለአንተ መሰደዱ።
በጸሎት በስግደት በፆም ተጋድሎ፣
ሰይጣንን ድል ነስቶ ወደ ጥልቁ ጥሎ፣
መኖር እንዲህ ነበር አንተን ብቻ ብሎ።
ገዳሙ ገዳሙ ሰምተሃል? ገዳሙ፣
ለልማት ይመንጠር ብሎሃል ዓለሙ።
በዚህ ትስማማለህ? መልስ ስጥ ገዳሙ፣
ልማት አይደለም ወይ? ጸሎቱና ፆሙ።
ይህንን ከመስማት ደግሞም ከማየት፣
የዓለምን ጥላቻ ኩርፊያ ለመርሳት፣
ለኃጢአት ሞተን ኖረን ለሕይወት፣
መኖር እንዲህ ነበር መንኖ በእውነት።
ከቀሲስ ዲበኩሉ በላይ
ግንቦት 29/2007