Sunday, July 27, 2014

አራት ሚስቶች

አራት ሚስቶች ያሉት አንድ ሰው ነበር።

አራተኛዋን ሚስቱን ከሁሉም አስበልጦ ይወድዳት፥ ይንከባከባትም ነበር።

ሶስተኛዋን ሚስቱንም ይወድዳት፥ ለጓደኞቹም ያሳያት ነበር። ነገር ግን “እኔን ጥላኝ፡ ከሌላ ወንድ ጋር ትኮበልላለች” ብሎ ሁሌም ይሰጋ ነበር።

ሁለተኛዋን ሚስቱንም ይወድዳት፡ ችግር በገጠመውም ግዜ ሁሉ ያዋያት ነበር፤ እሷም ሰለቸኝ፡ ደከመኝ ሳትል ዘወትር ትረዳው ነበር።

የመጀመሪያዋን ሚስቱን ግን ጭራሽ አይወድዳትም ፤ እርሷ ግን በተቃራኒው ከልብ ታፈቅረዋለች።

ከእለታት አንድ ቀን፡ ሰውዬአችን በጠና ታመመ፤ በህይወት ብዙም እንደማይቆይ ተረዳ።

“አራት ሚስቶች አሉኝ፤ ከሞትኩ በኋላ ብቸኝነት እንዳያጠቃኝ አንዷን ይዤ እሄዳለሁ።” ብሎም ወሰነ።

በዚህም መሰረት አራተኛውን ሚስቱን አብራው እንድትሞትና ከብቸኝነቱ እንድታስጥለው ጠየቃት።

“በጭራሽ አይሆንም!” ብቻ ብላ ሌላ ቃል ሳትተነፍስ ጥላው ሄደች።

ሶስተኛ ሚስቱን ተመሳሳይ ጥያቄ ሲጠይቃት

“እዚህ ህይወት ተመችቶኛል፤ ከሞትክ በኋላ ሌላ ባል አግብቼ እኖራለሁ” ብላ ተቃወመች።

ፊቱን ወደ ሁለተኛዋ ሚስቱ ቢያዞር

“አዝናለሁ! አሁን ልረዳህ አልችልም፤ ቢበዛ እስከ መቃብርህ ብከተልህ ነው።” ብላ አሳፈረችው።

ይህንን ተደጋጋሚ እንቢታ ሲሰማ፡ ልቡ በሀዘን ቀዘቀዘች።

ነገር ግን፡ ከጸጥታውና ከሀዘኑ መሀል፡ አንድ ድምጽ እንዲህ አለው፦

“እኔ አብሬህ እሄዳለሁ፤ የትም ብትሄድ እከተልሀለሁ።”

ሰውየው ቀና ቢል፡ ታማኝ ወዳጁን፡ የመጀመሪያ ሚስቱን ተመለከተ።

በቂ ምግብ ያላገኘች ሰው ትመስል በጣም ከስታናና ገርጥታ ነበር።

ድምጹ በከባድ ሀዘን እየተሰባበረ

“በጤና እያለሁ፡ የበለጠ ልንከባከብሽ ይገባኝ ነበር!” አላት።

እንደ እውነቱ ከሆነ፡ ሁላችንም አራት ሚስቶች/ባሎች አሉን።

1. አራተኛ ሚስት/ባል ሰውነታችን ነው።

ምንም ያህል ብንንከባከበው፡ ስንሞት አይከተለንም።

2. ሶስተኛ ሚስት/ባል ሀብትና ንብረታችን ነው።

ስንሞት ለሌሎች ይተላለፋል።

3. ሁለተኛ ሚስት/ባል ዘመድ ወዳጆቻችን ናቸው።

በህይወት እያለን ምንም ያህል ቅርቦቻችን ቢሆኑም፡ ከመቃብር ባሻገር አይከተሉንም።

4. የመጀመሪያ ሚስት/ባል ነፍሳችን ናት።

በምድር ላይ ቆይታችን ሀብትን እና ዝናን ስናሳድድ ችላ እንላታለን። በሄድንበት ቦታ ሁሉ አብራን የምትሄደው ግን እርሷው ብቻ ናት።

ስለዚህ ንስሀ እንግባ
ስለዚህ ንስሀ እንግባ
ስለዚህ ንስሀ እንግባ

No comments:

Post a Comment