Monday, August 26, 2013

በጎች እና ፍየሎች

አንድ ጊዜ በጎች እና ፍየሎች ከተለያየ አገር ለቅቀው ሲሄዱ ከሁለት ወገን የመጡት በጎች እና ፍየሎች አንድ ድልድይ ላይ ደረሱ፡፡ ድልድዩ ከወዲያ ወደዚህ ለመሻገር የሚቻለው በአንድ ጊዜ መሆኑን የድልድዩ ባለቤት ተናገረ፡፡ ከሁለቱም በኩል የመጡት በጎች በአንድ ላይ፣ ከሁለቱም በኩል የመጡት ፍየሎችም በአንድ ላይ፡፡
የሚያሳዝነው ግን ድልድዩ ሊያሳልፍ የሚችለው አንድ በግ ወይንም አንድ ፍየል ብቻ ነው፡፡ የሚፈቀደው ግን ከሁለቱም አቅጣጫ ሁለት በጎች ወይንም ሁለት ፍየሎች እንዲገቡ ነው፡፡
የመጀመርያው ዕድል ለፍየሎች ተሰጠ፡፡ ሁለት ፍየሎች ወደ ድልድዩ ከተለያየ አቅጣጫ ቀረቡ፡፡ እኔ ቀድሜ ማለፍ አለብኝ በሚል ሁለቱም ተጣሉና በቀንዳቸው መዋጋት ጀመሩ፤ በመጨረሻም ሁለቱም ወደ ወንዙ ወደቁ፡፡ ሌሎች ሁለት ፍየሎችም ሄዱ፡፡ እነዚህም ማን ይቅደም በሚለው ስላልተስማሙ ተዋጉ፡፡ ወንዝ ውስጥም ወደቁ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ ሁሉም ፍየሎች እየተዋጉ ወንዝ ውስጥ እየገቡ አለቁ፡፡
ቀጥሎም የበጎች ተራ ደረሰ፡፡ ሁለት በጎች ወደ ድልድዩ ከተለያየ አቅጣጫ ቀረቡ፡፡ ተነጋገሩ ተግባቡ፡፡ አንዱ በግ ተኛ ሌላው በላዩ ላይ አለፈ፡፡ ያኛውም ተነሥቶ አለፈ፡፡ እንደዚሁ ሌሎች በጎችም እየተነጋገሩ አንዱም እየተኛ፣ ሌላውም በላዩ ላይ እያለፈ፤ ያለምንም ችግር በጥቂት መቻቻል ተሻገሩ፡፡
ችግሮችን በመፍታት አካሄድ ይህ የበጎች እና የፍየሎች ሁኔታ እንዴት ይተረጎማል? በትዳር፣ በንግድ ሽርክና፣ በማኅበር፣ በድርጅት፣ በፓርቲ፣ በኮሙኒቲ፣ በቤተሰብ፣ ወዘተ ወዘተ፣ እንወያይበት

No comments:

Post a Comment